“ክለቦች ዘንድሮ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ከአንድ ዓመት በላይ ማስፈረም አይችሉም”

የትኛውም ክለብ ዘንድሮ ከአንድ ዓመት የውል ዘመን በላይ የውጪ ተጫዋቾች ማስፈረም እንደማይችል ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በቅርቡ ለክለቦች ረቂቅ የዝውውር መመሪያ ደንብን አውጥቶ ለክለቦች በሀምሌ ወር መጨረሻ እንዲወያዩበት እና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ በሰነድ መልክ ማቅረቡ ይታወቃል። የቀረበውንም ሰነድ ክለቦች ተመልክተው መልስን እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ የመጨረሻ ቀን ቆርጦ መልሳቸውን እንዲልኩ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ በዚህ ደንብ ላይ በተለይ ከዘንድሮው የ2013 የውድድር ዘመን ጀምሮ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ቁጥር ከአምስት ወደ ሦስት እንዲሁም ደግሞ ዜግነታቸው ከኢትዮጵያ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾችን በሊጋችን መኖር የለባቸውም የሚሉ ሀሳቦችን ያዘለ ደንብም እንደነበረ ከዚህ ቀደም በዘገባችን መግለፃችን ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዝውውር መስኮቱ ዛሬ በይፋ በመከፈቱ ክለቦች በዚህ ደንብ መሠረት ነው የሚተዳደሩት ወይስ በቀደመው አሰራር ይቀጥላሉ የሚሉ ጥያቄያዎች ተሰንዝረዋል። በዚህ ዙርያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ክለቦች በነበረው የቀደመው ደንብ መሠረት የውጪ ተጫዋቾችን ማስፈረም ይችላሉ። ግን ዘንድሮ የውጪ ተጫዋቾችን ከአንድ ዓመት የውል ርዝመት በላይ ማስፈረም የተከለከለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

“ለክለቦች ሰነድ ልከን መልስ የሰጡን ጥቂት ክለቦች ናቸው፡፡ በጣም ትንሽ ክለብ ነው የራሱን መልስ የሰጠን። በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው ምላሻቸውን የላኩልን፡፡ እንደ ስራ አስፈፃሚ ስንነጋገር ሰርኩላር ለመስራት አስበናል። ለምሳሌ የውጪ ግብ ጠባቂ አንድ ክለብ ቢኖረው ለዘንድሮው ብቻ ወይንም ከአንድ ዓመት በላይ አይፈርምም። ሌሎች የውጪ ተጫዋቾችም ከአንድ ዓመት በላይ አይፈርሙም፤ ቁጥራቸው ይገደባል። ይሄ ደግሞ ከ2014 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!