ሪፖርት | የሸገር ደርቢ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ሪፖርት | የሸገር ደርቢ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ቡናማዎቹ በሁለቱም አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታጅበው ፈረሰኞቹን 2ለ0 በማሸነፍ በውድድሩ ዓመቱ ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቀቻውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በ34ኛው ጨዋታ ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር 1ለ1 ሲለያዩ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ዋሳዋ ጂኦፍሪን እና ኤርሚያስ ሹምበዛን አሳርፈው በምትካቸው ገዛኸኝ ደሳለኝን እና ሚኪያስ ፀጋዬን ተክተው ሲገቡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ይዘው ከገቡት ከመጀመሪያው ቋሚ ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ቶሎሳ ንጉሤን በሄኖክ ዮሐንስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከበርካታ ደጋፊዎች ጋር ታጅቦ የተካሄደው የሸገር ደርቢ ሁለቱም ቡድኖች ቀዳሚ ለመሆን በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጥረት ያደረጉበት ቢሆን ጥራት ያላቸውን ኳሶች ወደ ሳጥን ይዘው መግባት አልቻሉም። ጨዋታው ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በቅርቡ ከዚህ ዓለም ድካም ላረፈው ለቀድሞው ተጫዋቻቸው ሙሉጌታ ከበደ መታሰቢያ ሁሉም የቡድኑ አባላቶች እንዲሁም ደጋፊዎች ቆመው ያጨበቸቡላቸው ክስተት ይጠቀሳል።

እንደተጠበቀው በሙከራዎች ጋር ሳይታጀብ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ የኳስ ቅብብል ያደረገ ቡድን ነበር። በዚህም ኳስ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል መስርተው እየተጫወቱ ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ሲደርሱ አስተውለናል። ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ልክ ከተጋጣሚዎቻቸው ተቃራኒ በሆነ መንገድ በመስመር በኩል ሰብረው ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጫና አሳድረው ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በወሰዱበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያቸውን ሙከራ 8ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ራምኬል ጀምስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ባይጠብቅም ተጠቃሽ ነበር። የአጋማሹ አካፋይ ድረስ ባለው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ፊት በመሄድ ጥረቶችን አድርገዋል ሆኖም ግን አንድም የጠራ ሙከራ ሳያደርጉ በጨዋታው ሃያ አምስት ደቂቃዎች ተቆጥረውበታል።

ምንም እንኳን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ባላስመለከተው በዚህ ጨዋታ ቡናማዎቹ በመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል፤ 28ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ አግኝተው ናይጀሪያዊው የመሃል ስፈራ ተጫዋች ዲቫይን ዋቹኩዋ ኳሱን ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ፈረሰኞቹ በእንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆኑም በሙከራዎች ጋር የታጀበ አጨዋወት ማድረግ ባልቻሉበት በመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሆን ተስኗቸው የጨዋታ ብልጫ በተጋጣሚዎቻቸው ተወስዶባቸዋል። እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሆን የተሳናቸው ፈረሰኞቹ ግቡ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ 31ኛው ደቂቃ ላይ ሻይዱ ሙስጠፋ የቆመ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ዳንላድ ኢብራሂም በቀላሉ ከጥቆጣጠረባቸው ሙከራ ውጪ በአጋማሹ ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

መሪነታቸውን ያረጋገጠች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ይበልጥ ወደ ፊት ተጠግተው ተጨማሪ ግብ የሚሆኑ ግቦችን ለመፍጠር ሲጣጣሩ የነበሩት ቡናማዎቹ  ጨዋታው 34ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የፈረሰኞቹ ተከላካይ አሸናፊ ጌታቸው በሰራው ስህተት ኮንኮኒ ሀፊዝ ኳስ ቀምቶ ወደ ሳጥን የገፋውን ኳስ ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና ደርሶ ባይቆጣጥረው ባልተጠበቀ መልኩ ሁለተኛ ግብ ለማግኘት የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር። እንዲሁም 40ኛው እና 41ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎች ያደረጓቸው ሙከራዎች ሲታወሱ በጥሩ ቅብብል ከሳጥን ውጪ የተገኘውን ዲቫይን ዋቹኩዋ ቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ለጥቂት ከግቡ ርቆ ሲያልፍበት ራሱ ዲቫይን በተከላካይ ጀርባ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ኮንኮኒ ሀፊዝ ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ባህሩ ነጋሽ እንዴትም ቀድሞ ያወጣባቸው ሌላኛው አደገኛው አጋጣሚ ይጠቀሳል። አጋማሹም በቡናማዎቹ የበላይነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው የተመለሱት ፈረሰኞቹ አጋማሹ እንደተመለሰ 46ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፣ ቢኒያም ፍቅሩ ያገኙትን ቅጣት ምት አክርሮ ወደ ግብ ሲመታት ግብ ጠባቂው አግዶበታል። የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በሁለተኛ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ያደረጉት ቡናማዎቹ 49ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ በተጣለ ኳስ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ ሙከራ አድርገዋል፣ ግብ ጠባቂው በረጅሙ የለጋውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ወደ ግብ ሲመታው  ባህሩ ነጋሽ ጨርፎ አውጥቶባቸዋል።

ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል፤ ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ የፈረሰኞቹን ተከላካዮች አታሎ አልፎ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ግብ የመታውን ኳስ አሸናፊ ጌታቸው እና ባህሩ ነጋሽ ላይ ተጨራርፎ ኳሱ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ እንዲል ሆኗል።

ፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብሎም  በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን እየደረሱ የቡናማዎቹን ተከላካይ መስመር ሲፈትኑ ያስተዋልን ሲሆን በተለይም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፉዓድ አብደላ አግኝቶ ሳይጠቀም የቀረባቸው ሁለት ደካማ ሙከራዎች ይታወሳሉ። እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው በሙሉ ኃይላቸው ሲያጠቁ የነበሩት ፈረሰኞቹ 85ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተው አምክነዋል፣ በጥሩ ቅብብል ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ ገብተው ፉዓድ ለበረከት ወልዴ ያቃበለውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረበት አጋጣሚ ይታወሳል።

የሁለት የግብ ልዩነት አግኝተው መሪነታቸውን ያጠናከሩት ቡናማዎቹ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያድርጉ የተመለከትን ሲሆን 76ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው ስንታየሁ ዋለጨ በመጀመሪያ ንክኪው ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገውን ጠንካራ ሙከራ ባህሩ ነጋሽ እንዴትም ጨርፎ ያውጣው እንጂ ተጨማሪ ግብ ለመሆን እጅጉን የቀረበ ሌላኛው ሙከራ ነበር።

89ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሳይጠበቅ ሶስተኛውን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም አማኑኤል አድማሱ አምክኖታል። እንዲሁም ፈረሰኞቹም መደበኛው የጨዋታ ተጠናቆ ጭማሪ የታየው ላይ አማኑኤል ኤርቦ በቅብብል የተገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ሌላኛው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል ተጠቃሽ ነበር። ጨዋታው ተጨማሪ ግቦች የሚቆጥርበት እየመሰለ ወደ መገባደጀው የዘለቀ ቢሆንም ይህኛው የሸገር ደርቢ ለቡናማዎቹ ሙሉ ሦስት ነጥብ ከሁለት ንፁህ ግብ ጋር በማጎናፀፍ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጠ አስተያየት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ደርቢን ማሸነፉ ከዋንጫ ያልተናነሰ የሚሰጠው ደስታ እንዳለ አንስተው ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዋንጫ ቢገባቸውም የአቅማቸውን እንደሰጡና ዛሬ ተጫዋቾቹ ባደረጉት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ከእነሱ ይልቅ ተጋጣሚያቸው ግብ አከባቢ በሚደረጉ አጨራረስ የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረው ጨዋታው በአጠቃላይ ባሰቡት መንገድ እንዳልሄደላቸው እና ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ረገድ ደካማ እንደነበሩ ተናግረዋል