አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ በክለቡ የሚሰሯቸውን ስራዎች ገለፃ ሲያደርጉ ክለቡ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ከሀገር ውጪ ወጥቶ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ተናገሩ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የቴክኒክ ዳይሬክተር፣ የአሠልጣኝ እንዲሁም የአዳዲስ ተጫዋቾች ትውውቅ መርሐ ግብር እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የቡድኑ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ሚቾ ክለቡን እያደራጁ የሚገኙበትን መንገድ እንዲሁም በቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ወቅት የሚሰሯቸውን ስራዎች በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በማብራሪያቸው ወቅት ቡድኑ በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ከሚያደርገው ዝግጅት ጎን ለጎን በምስራቅ አፍሪካ ሀገር ሁለት ወይም ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
ቡድኑ ስለሚያደርገው የምስራቅ አፍሪካ የዝግጅት ጊዜ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ያልተሰጠ ሲሆን ከላይ እንደተገለፀው ከማን ጋር እንደሆነ ባይገለፅም ሁለት ወይም ሦስት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግና ለሊጉ እንደሚዘጋጅ ተጠቅሷል። ከምስራቅ አፍሪካው ጉዞ መልስ ቡድኑ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ተሳትፎ በሊጉ እንደሚቀርብ ተመላክቷል።
አሠልጣኝ ሚቾ ከሹመቱ በኋላ የሰጡትን አስተያየት እንዲሁም ስለዝግጅት ጊዜያቸው የሰጡትን ሰፊ ማብራሪያ ከቆይታ በኋላ ይዘን እንቀርባለን።

