ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሁኑ ሰዓት እየሰጠ ከሚገኘው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሁም የቴክኒክ ዳይሬክተር እና የአሠልጣኝ ትውውቅ ላይ እየተሰሩ ያሉትን አሁናዊ ስራዎች በተመለከተ የተሰጠውን ማብራሪያ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

በቅርቡ ስለተጀመረው የኦዲት ስራ እና ስለ ስፖርት ፋሲሊቲ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጊዜያዊ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ነሲቡ ጫኮ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ግንቦት 16 አዲሱ ቦርድ ከተመረጠ በኋላ ስራዎች የተጀመሩት ሰኔ ወር ላይ እንደሆነ የተናገሩት የቦርድ ሰብሳቢው ክለቡ ከነበረበት የፋይናንስ ችግር እንዲያገግም ስራዎችን እንደሰሩ አመላክተዋል። በተለይ በአስተዳደር ችግር ምክንያት በመንግስት የተወሰደውን መሬት ለማስመለስ ጥረቶች እንደተደረጉ አመላክተው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኙትን ሁለት ሜዳዎች የግንባታ ፍቃድ ለመውሰድ ጥረቶች እንደተደረጉ በተለይ ትልቅ ይዞታ ያለውን ቦታ እንደሚመለስ ትልቅ ተስፋ አለን ብለዋል። ሰብሳቢው ጨምተው “ቦታው እንደተሰጠንም በ2019 ሚድሮክ ሜዳውን እንዲሰራልን እናደርጋለን። ይህ ሜዳ እስኪሰራ ድረስም ዋናው ቡድን ቢሾፍቱ በሚገኘው አካዳሚ አርፎ ዝግጅቱን ይቀጥላል። አካዳሚው ለዋናው ቡድን ባይዘጋጅም ዋናው ሜዳ እስኪዘጋጅ ድረስ ቡድኑም በሚቀጥለው ማክሰኞ ገብቶ ዝግጅቱን ይጀምራል።” ብለዋል
የፅህፈት ቤቱን የማደራጀት ስራ በተመለከተ የውጪ ኦዲተር መጥቶ ስራዎችን እየሰራ ነው። ኦዲቱ ካለቀ በኋላ ቀጣይ ሀሳቦችን እናስቀምጣለን ያሉት ጊዜያዊ ሰብሳቢው የደጋፊ ማኅበር ሊቋቋም መሆኑን አመላክተው። በማቋቁም ሂደት ላይ ችግሮች ካሉ ለመርዳት ዝግጁ በማለት ይህ የደጋፊ ማኅበር ክለቡን እንዲያግዝ ነው የምንፈልገው የሚል ንግግራቸውን አሰምተዋል።
ክለቡም ገንዘብ እንዲያመነጭ ኦዶ የሚባለወ ሲስተም ለመጀመር ዝግጅት ላይ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በተለይ የሽያጭ ሂደት እና መሰል ነገሮችን እንዲቆጣጠር የሚያስችል ሲስተም እየተሰራ መሆኑንና የኢአርፒ ሲስተም መስከረም ላይ ተጠናቆ ይፋ ይሆናል። ፅህፈት ቤቱን በባለሙያዎች ለማደራጀት እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
በመጨረሻም “የገንዘብ ችግር የለብንም ፤ የፈለግነው ሁሉ እየተሰጠን ነው።” በማለት አቶ ጀማልን አመስግነው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

