ሚቾ በይፋ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ሆነዋል

ሚቾ በይፋ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ሆነዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾን በአምስት ዓመት ውል የቡድኑ አሠልጣኝ አድርጎ ሾመ።

በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቴክኒክ ዳይሬክተር እና የአሠልጣኝ ትውውቅ መርሐ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ቀደም የተገለፀው የአሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ሾመትም ይፋ ሆኗል።

በዚህም ሰርዲዮቪች ሚሉቲን (ሚቾ) ለተጨማሪ ዓመታት ሊታደስ የሚችል የአምስት አመታት ውል ፈርመዋል፡፡ የዋናው ቡድናችን ዋና አሰልጣን ሆነው የተሾሙት አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን (ሚቾ)እ.ኤ.አ ከ2004-2006 እንዲሁም ከ2007-2010 ድረስ በአጠቃላይ ለአምስት አመታት ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሰልጠን አምስት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲሁም ሌሎች ታላላቅ ዋንጫዎችን ማሸነፍ የቻሉ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ በአሁኑ ወቅት የ57 አመት ጎልማሳ ሲሆኑ በአፍሪካ እግር ኳስ የዳበረ ልምድ ያላቸው አንጋፋ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ሚቾ ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮ በአፍሪካ በርካታ ክለቦችና ብሄራዊ ቡድኖችን ያሰለጠኑ ሲሆን ስኬታማ ከሚባሉ አሰልጣኞች ተርታ የሚሰለፉም ናቸው፡፡ በአፍሪካ ቆይታቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈ የግብጹን ዛማሌክ ፥ የደቡብ አፍሪካውን ኦርላንዶ ፓይሬትስ ፥ የአልጄሪያውን ሴቲፍ፥ እንዲሁም የሱዳኑን አልሂላል ያሰለጠኑ ሲሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሊቢያ ፥ ዩጋንዳ ፥ ሩዋንዳ ፥ ዛንቢያን አሰልጥነዋል፡፡