አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው በይፋ ተሾሙ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሁኑ ሰዓት የቴክኒክ ዳይሬክተር እና የአሠልጣኝ ትውውቅ መርሐ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን አሠልጣኝ ሥዩም ከበደን የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር እንዲሁም የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ስራ አስኪያጅ አድርጎ ሾኗል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንዲያገለግሉ የቴክኒክ ዳይሬክተር አድርጎ የሾማቸው የቀድሞ ተጫዋቹና አሰልጣኙ ኢንስትራክተር ሥዩም ከበደ ነው። አሠልጣኝ ሥዩም በአሰልጣኝነትም በተለይም በብዙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሚታወሰውን ታሪካዊውን የ1995 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አንስተዋል፡፡ ኢንስትራክተር ስዩም ሹመቱን አስመልክተው “ይህ የሥራ ድርሻ ለእኔ በጣም አጓጊ ነው፡፡አሁን ሳይንሱና ታዳጊዎች ላይ የሚያተኩር ሥራ ለመስራት እድል አግኝቻለሁ፡፡ ሥራዬ ቅዱስ ጊዮጊስን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚጠቅም ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲህ አይነት ወሳኝ እድል ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ” በማለት ተናግረዋል፡፡
አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ከቴክኒክ ዳይሬክተርነት ስራቸው በተጨማሪ የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ስራ አስኪያጅ እንደሆኑም ተመላክቷል።

