የሽመልስ በቀለ ማረፊያ ታውቋል።
ከቀናት በፊት ሶከር ኢትዮጵያ ባስነበበችው መሰረት ስኬታማው አማካይ ሽመልስ በቀለ ወደ እናት ክለቡ ሀዋሳ ከተማ ሊመለስ እንደሚችል ጠቁመን ነበር። በዚህም መነሻነት ሽመልስ በቀለ ዛሬ በይፋ የሀዋሳ ከተማን ተጫዋች መሆኑ ተረጋግጧል። አስቀድመው አብነት ደምሴን ያስፈረሙት ሀይቆቹ ሽመልስ ሁለተኛ ፈራሚያቸው ይሆናል ማለት ነው።
የእግርኳስ ህይወቱን በኮረም ሜዳ የጀመረው አማካዩ ሽመልስ በቀለ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨምሮ በክለብ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ በማስከተል ከሀገር ውጭ ለሱዳኑ ኤል ሜሪክ እና አል ኢትሀድ እንዲሁም ወደ ግብፅ በማቅናት ለግብፆቹ ክለብ ፔትሮጀት (አምበል ) ፣ ኤል ጉና፣ ምስር አልመካሳ እና ኤንፒ በመጫወት የፕሮፌሽናል የእግርኳስ ህይወቱን ከመራ ከአስር ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ለመቻል ሁለት ዓመታት መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ማረፊያው የቀድሞ ክለቡ ሀዋሳ ይሆናል ማለት ነው።
