ሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከነማ ድል ቀንቷቸዋል

ሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከነማ ድል ቀንቷቸዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ4 ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ላይ ሲዳማ ቡናና ፋሲል ከነማ አሸነፉ

ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ተጠባቂው ጨዋታ ገና ከጅማሮው በቀይ ካርድ የታጀበ ሲሆን የወላይታ ድቻው ናትናኤል ናሴሮ በ5ኛው ደቂቃ የሲዳማው ቡናው ተጫዋች ብለሥ ናጎ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ያለውን የቁጥር ብልጫ የተጠቀሙት ሲዳማ ቡናዎችም ብዙም ሳይቆዩ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከቀኝ መስመር ብርሃኑ ያሻገረውን ኳስ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ብልጫ ወስደው መጫወት የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች 39ኛው ደቂቃ ላይም በፍራኦል መንግስቱ የቅጣት ምት ሙከራ ቢያደርጉም አጋማሹ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

ቀዝቀዝ ያለ እንዲሁም ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ በጥፋቶች ታጅቦ የተከናወነ ነበር። በአጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግ ከቆየ በኋላም መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጡ ተጨማሪ ደቂቃዎች የሲዳማ ቡናው መላኩ አሰፋ ከርቀት አክርሮ በመምታት ከመረቡ ጋር ባዋሀዳት ግብ ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን በሁለት ለባዶ አሸናፊነት አጠናቀዋል።

ፋሲል ከነማን ከ ምድረ ገነት ሽረ ፋሲል ከነማ እና ምድረ ገነት ሽረ ያገናኘው የአመሻሽ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። አቤል ማሙሽ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቷት ሞየስ ፓዋቲ ግብ ከመሆን የታደጋት ሙከራም በአጋማሹ የተሻለ ለግብ የቀረበች የመጀመርያ ሙከራ ስትሆን በ34′ ደቂቃ ግን በጨዋታ እንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች አምሳሉ ጥላሁን ከተከላካይ ጀርባ አሻግሯት ቃልኪዳን ዘላለም በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት በቀየራት ኳስ መሪ መሆን ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ ምድረ ገነት ሽረዎች የተወሰደባቸውን የግብ ብልጫ በመቀልበስ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ነገር ግን በቁጥር በርከት ብለው ከራሳቸው የግብ ክልል በጥንቃቄ መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉትን የፋሲል ከነማ ተከላካዮች አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በቃልኪዳን ዘላለም ብቸኛ ግብ ዐፄዎቹ አሸናፊ ሆነዋል።