ሪፖርት | መቻል እና ፋሲል ከነማ መሪነቱን የሚረከቡበትን ዕድል አባክነዋል

ሪፖርት | መቻል እና ፋሲል ከነማ መሪነቱን የሚረከቡበትን ዕድል አባክነዋል

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ6ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል።

ምድረ ገነት ሽረ ከ መቻል

በዋና ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ መሪነት በተካሄደው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ መቻል የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ መያዝ ሲችል ሙከራዎች በማድረግ ብልጫ የነበረው ግን ሽረ ምድረ ገነት ነበር። ናትናኤል ተኽለ እና ዳንኤል ዳርጌ በተመሳሳይ ቦታ ከሳጥን ውስጥ ያደረጉት እና አልዮንዜ ናፍያን ወደ ውጭ ያወጣቸው ሙከራዎች እንዲሁም ስንታየሁ ዋለጬ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።  በ18ኛው ደቂቃም ሽመክት ጉግሳ ከመስመር አሻግሯት ዳንኤል ዳርጌ ወደ ግብነት በቀየራት ኳስ ምድረገነት ሽረዎች መምራት ጀምረዋል።

በአጋማሹ አመርቂ የፊት መስመር እንቅስቃሴ ሳያደርጉ የቆዩት መቻሎች በ33ኛው ደቂቃ ግን ዳዊት ማሞ ከመስመር አሻግሯት በረከት ደስታ በግንባር ባስቆጠራት ግብ አቻ ሆነዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም አብዱልከሪም ወርቁ  ከመስመር ተሻግራ ኮሊን ኮፊ ያመቻቻትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ በማስቆጠር ጦሩን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ እንዲሁም ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። አጋማሹ በተጀመረ በአስር ደቂቃዎች ውስጥም ሽረዎች የአቻነቷ ግብ አስቆጥረዋል፤ በኃይሉ ግርማ በግብ ጠባቂው ስህተት የተገኘችውን ኳስ ለአቤል ማሙሽ ካመቻቸለት በኋላ አጥቂው አክርሮ  በመምታት ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን አቻ ማድረግ ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ያብስራ ተስፋዬ ከመዓዝን የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የምድብ አንድ የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በመጀመርያው አጋማሽ የፋሲል ከነማዎች ሙሉ ብልጫ የታየበት ሲሆን ዐፄዎቹ በርከት ያሉ ሙከራዎችም ማድረግ ችለዋል። ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ሞክሯት ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳየ ባዳናት ኳስ ጥቃታቸው የጀመሩት ዐፄዎቹ ዳግም አወቀ ከርቀት አክርሮ ባደረገው እንዲሁም በረከት ግዛው ከናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ግብ ጠባቂው በመለሳት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። አቤል ነጋሽ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቷት በሞየስ ፖዊቲ የተመለሰች ሙከራም በድሬዳዋ ከተማ በኩል የምትጠቀስ ሙከራ ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ በፈጣን ሽግግሮች በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ቢሆንም ወደ ሙከራነት የተቀየሩ ኳሶች ግን ጥቂት ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ባደረጉት ብርቱካናማዎቹ በኩል አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት ሞየስ ፖዊቲ ወደ ውጭ ያወጣው ድንቅ ሙከራ ተጠቃሽ ስትሆን ውስን መቀዛቀዝ ባሳዩት ዐፄዎቹ በኩል ደግሞ ቃልኪዳን ዘላለም በደረቱ አብርዶ ከርቀት ያደረጋት ጥሩ ሙከራ ትጠቀሳለች። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።