ሪፖርት| ሀይቆቹ ጣፋጭ ድል ሲጎናፀፉ መቐለ 70 እንደርታና ሸገር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ሀይቆቹ ጣፋጭ ድል ሲጎናፀፉ መቐለ 70 እንደርታና ሸገር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሀዋሳ ከተማ በሽመልስ በቀለ ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ አዝናኝ የነበረው የመቐለ 70 እንደርታ እና የሸገር ከተማ ጨዋታ 0 – 0 ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሀይቆቹ ከፈረሰኞቹ ባገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ቡድኖቹ ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የተጋሩበት እንዲሁም እጅግ ቀዝቃዛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር።

አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በተደረገበት አጋማሽ በአንፃራዊነት የተሻለ የፊት መስመር እንቅስቃሴ የነበራቸው ፈረሰኞቹ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የፈጠሯት የግብ አጋጣሚም ተጠቃሽ ናት። ፀጋ ከድር በ38ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣችው ሙከራም ብቸኛዋ የአጋማሹ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደረገበት እንዲሁም በድምሩ 21 ጥፋቶች የተሰሩበት አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

ሁለቱም ቡድኖች ተሻሽለው የቀረቡበት ሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። አጋማሹ በተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላም ሽመልስ በቀለ ከተከላካይ ጀርባ የተሻገረችለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ከመረብ ጋር በማዋሀድ ሀይቆቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ልዩነት ከፈጠረች ግብ በኋላም ፈረሰኞቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና በመፍጠር በሀብታሙ ጉልላት አማካኝነት ሁለት ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ተጫዋቹ በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ መቶ ከግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣችበት እንዲሁም ከሳጥኑ ጠርዝ መሬት ለመሬት መቷት ሰይድ ሀብታሙ የተቆጣጠራት ኳስም ፈረሰኞቹን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

በቀሩት ደቂቃዎች ሀይቆቹ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ፈረሰኞቹ ግን የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው በመጫወት በባከኑ ደቂቃዎች ወርቃማ ዕድል ማግኘት ችለዋል። ተገኑ ተሾመ በረዥሙ ተሻግራ ሰይድ ሀብታሙ የጨረፋትን ኳስ አግኝቶ ከመታቱ በፊት ግብ ጠባቂው እንደምንም ያዳናት ኳስም ፈረሰኞቹን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታም ሐይቆቹ በሽመልስ በቀለ ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 ማሸነፍ ችለዋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ሸገር ከተማ

በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙ ቡድኖችን ያፋለመው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ አዝናኝ ፉክክር ያስመለከን ነበር።

ቡድኖቹ በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ባደረጉበት አጋማሽ ላይም ምዓም አናብስት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ብርሃኑ አዳሙ ብቻውን ሳጥን ውስጥ አግኝቶ መቷት ባህሩ ነጋሽ እና ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ኳስ እንዲሁም ፍፁም ዓለሙ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ባህሩ ነጋሽ ያዳናት ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።
በሸገር ከተማዎች በኩልም አንተነህ ተፈራ ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ምስጋና ሚልክያስ በመቀስ ምት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳል።

በተመጣጣኝ ፉክክር እና ማራኪ እንቅስቃሴ ታጅቦ የተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ ሳቢ ፍልምያ የተደረገበት ነበር። ለተመልካች ሳቢ የነበረው እና በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች በተፈጠሩበት አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች ያለቀላቸው የግብ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል።

በአጋማሽ ተሻሽለው በቀረቡት ሸገር ከተማዎች በኩል ሙአዝ ጋሊ ከቡልቻ ሹራ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከግቡ ቅርብ ርቀት መሬት ለመሬት በመምታት ያደረጋት ሙከራ፤ አንተነህ ተፈራ በመቐለ ተከላካይ ስህተት ያገኛትን ኳስ ተከላካዮች አልፎ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት እንዲሁም በዛ ሂደት ውስጥ ራሱ አንተነህ አሻምቷት
ቡልቻ ሹራ በግንባሩ ገጭቷት በድጋሜ መሀመድ ዛጉዬ የመለሳት ኳስ ሸገር ከተማዎችን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።

ከጨዋታው መገባደጃ ላይ የተሻለ ጫና በፈጠሩት ምዓም አናብስት በኩልም ደስታ ዩሐንስ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ባህሩ ነጋሽ እንደምንም ባዳናት ኳስ እና ስንታየሁ መንግስቱ ከቆመ ኳስ ተሻግራ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ መቷት ተከላካዮች ተረባርበው ባወጧት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በሁለቱም አጋማሾች አዝናኝ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።