15ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ መርሐግብሮች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ መቻል
በ8 ነጥቦች ግርጌው ላይ የሚገኙት አዞዎቹ በመደዳ ከገጠሟቸው ሁለት ሽንፈቶች በኋላ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከሽንፈት መራቁ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች መረቡን አስከብሮ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ቢሆንም ከግርጌው ለመላቀቅ ከድል ጋር መታረቅ ግድ ይለዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ላይ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘት የቻለው የፊት መስመራቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
ቀስ በቀስ ከዋንጫ ፉክክሩ እየራቁ የሚገኙት መቻሎች በቅርብ ሳምንታት ከገጠማቸው የውጤት መጥፋት የሚያላቅቅ ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በ20 ነጥብ በ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከባለፉት አስር ጨዋታዎች ውስጥ ድል ማሳካት የቻለው በአንዱ ብቻ ነበር። ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በሚያከናውኑት የዛሬው ጨዋታም በሦስት መርሐግብሮች አምስት ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ማሻሻል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ20 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን መቻል 7 ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ 6 ጨዋታዎችን ሲያሸንፉ በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። አዞዎቹ 16 መቻሎች ደግሞ 17 ጎሎችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ፣ አሸናፊ ፊዳ እና በፍቅር ግዛቸው በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲታወቅ አንዱዓለም አስናቀ ግን ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። መቻል አማኑኤል ዮሐንስ ከጉዳት አልዮንዜ ናፍያንን ደግሞ ከአፍሪካ ዋንጫ ግዳጅ መልስ ሲያገኝ ውብሸት ጭላሎ እና ኮሊንስ ኮፊ ግን ባለማገገማቸው ከዛሬው ጨዋታ ውጪ እንደሆኑ ተመለክቷል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ
ተጠባቂ በነበረው መርሐ ግብር ፋሲል ከነማን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ካሉበት የደረጃ ሰንጠረዥ አካፋይ ከፍ ለማለት ሐይቆቹን ይገጥማሉ። ቡናማዎቹ ፋሲል ከነማ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና መቻል የመሳሰሉ ቡድኖች በገጠሙባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ቢችሉም በአንፃራዊነት ፈታኝ ባልነበሩ ቡድኖች ነጥብ ለመጣል ተገደዋል። ይህንን ተከትሎ በጨዋታዎቹ የተስተዋሉ ጥቂት የማይባሉ የመከላከል ድክመቶች በመቅረፍ ከዚህ ወጥነት የጎደለው አካሄድ መላቀቅ ከቡድኑ ይጠበቃል።
አንድ ድል ብቻ ካስመዘገቡባቸው አምስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ድሎች፣ አንድ አቻ እና አንድ ሽንፈት ያስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት ጥሩ መሻሻል አሳይተዋል። ሐይቆቹ በጨዋታዎች አስር ነጥቦች በመሰብሰብ በውጤት ረገድ ጥሩ ጉዞ በማድረግ ላይ ቢገኙም በተለይም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ያሳዩት እንቅስቃሴ መሻሻል የሚገባው ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ ጋር በተካሄዱ ጨዋታዎች አራት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስና መረብ ያገናኘውን የፊት መስመራቸው ወደ ቀድሞ ብቃቱ የሚመልስ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ከሊጉ የተሳትፎ ዝርዝር ጠፍተው የማያውቁት ክለቦቹ ከዚህ ቀደም ለ52 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና 18 ጊዜ ድል ሲያደርጉ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች 16 ድል አድርገዋል የተቀሩት 18 ግንኙነቶች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተደመደሙ ነበሩ። ኢትዮጵያ ቡና 64 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 55 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ
በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስድስት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ከድሬዳዋ ከተማ ይፋለማል። ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ፈረሰኞቹ በ8ኛው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ከረቱ በኋላ ድል ማድረግ አልቻሉም። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ያሳየው እንቅስቃሴ ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም ባለፉት አስር መርሐ ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የተሳነው የማጥቃት አጨዋወቱ ግን ሁለንተናዊ ለውጥ ይሻል።
17 ነጥብ በመሰብሰብ ከተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በኃላ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ከድንቅ እንቅስቃሴ ጋር ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለአንድ ካሸነፉበት የአስራ አንደኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳኩት ብርቱካማማዎቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በሦስት ተከታታይ መርሐ ግብሮች ግብ ማስቆጠር ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ26 ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 15ቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 5ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። ፈረሰኞቹ 40፣ ብርቱካናማዎቹ 20 ጎሎች አስቆጥረዋል።
አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
በ22 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከመሪዎቹ ጎራ ላለመራቅ ወሳኝ የሆነ ጨዋታ ያከናውናሉ። በቢንያም አይተን የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ሽረ ምድረ ገነትን ካሸነፉ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ነጥብ የተጋሩት አዳማ ከተማዎች አሁንም ውጤታማ የፊት መስመር ጥምረት ለማዋቀር ተቸግረዋል። በ14 መርሐ ግብሮች ውስጥ በአንድ ጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ የፊት መስመር ጥምረቱ የጥራት ደረጃ ከፍ ለማድረግ አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል።
በ29 ነጥቦች በሊጉ አናት የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ተከታዮቹ ነገሌ አርሲ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን የሚያሰፋበት ወርቃማ ዕድል አግኝቷል። ሸገር ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕናን በመደዳ ካሸነፉ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከተቀመጠው አርባ ምንጭ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሲዳማ ቡናዎች መሪነታቸውን ለማጠናከር እያለሙ በሚከውኑት የዛሬ ጨዋታ በሁለት መርሐ ግብሮች አራት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በ14ኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ መጠነኛ መቀዛቀዝ የተስተዋለበትን የፊት መስመራቸው ወደ ቀድሞ ብቃቱ የሚመልስ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 28 ጊዜያት ሲዳማ ቡና 9 አዳማ ከተማ ደግሞ 7 ጊዜ ድል ሲቀናቸው 12 ጨዋታዎች በአቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታተቻው ሲዳማዎች 23 አዳማዎችም በተመሳሳይ 23 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

