የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲካሄዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ምድረ ገነት ሽረ 0-0 በሆነ ውጤት ሲለያዩ መቻል ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ምድረ ገነት ሽረ
የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች ያልተረጋጋ በነበረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በራሳቸው የማጥቃት ዘዴዎች ተጠቅመው ግቦችን ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ምድረ ገነት ሽረዎች 12ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ተመልሶ ያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት አቤል ማሙሽ ከራሱ የሜዳ ክፍል በመነሳት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ገብቶ በግራ እግሩ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተጨርፎ ግብ ከመሆን ድኗል።
ከተጋጣሚ ተከላካዮች ጀርባ ነፃ የሆነ ቦታን ያጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 24ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ቢንያም ፍቅሩ ይዞ በመግባት ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ አቤል ያለው አመቻችቶ ለፍፁም ጥላሁን ያቀበለው ሲሆን ፍፁምም ከሳጥን ውጭ አክርሮ ቢመታውም ግብጠባቂው መልሶበታል።

ፈረሰኞቹ ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለው የቀረቡ ሲሆን በቢንያም ፍቅሬ የቅጣት ምት እና በፍፁም ጥላሁን የግንባር ኳስ ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 78ኛው ደቂቃ ላይ የምድረ ገነት ሽረ ተጫዋች ስንታየሁ ወለጨ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ የጨዋታው ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል።
ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ ያሳለፈው ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ የጨዋታው አነጋጋሪ የነበረው ክስተት ተፈጥሯል። 90+3 ላይ ፈረሰኞቹ መነሻን ከማዕዘን ምት ባደረገ የፍፁም ጥላሁን የግንባር ኳስ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም በዕለቱ ዋና ዳኛ አጨቃጫቂ ውሳኔ ግቡ ተሽሯል። ጨዋታውም ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ መቻል
ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው የምሽቱ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ መድኖች በመከላከሉ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የመቻልን የማጥቃት ዒላማዎች በተለያየ ዘዴ መመከት ችለዋል። በ36ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሐንስ ከመሐመድ አበራ ተቀብሎ ሳጥን ውስጥ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል እንደምንም ብሎ ግብ ከመሆን ታድጓታል።
የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሁለት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት የመድን መከላከል ላይ ውሃ የቸለሰ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በዚህም 43ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ አሻማውን ኳስ አለምብርሀን በግንባሩ ከገጨው በኋላ ቸርነት ጨርፎ መቻል ግብ አስቆጥሯል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መቻሎች መከላከልን ትልቁ ስራቸው በማድረግ በራሳቸው የግብ ክልል ላይ በቁጥር በዛ ብለው በመከላከል እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት በሚያገኟቸው ኳሶች ግብ ለማግባት አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። መድኖች በበኩላቸው የአቻነት ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ነገር ግን 56ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ በግንባር ገጭቶ ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ነጥሮ ከወጣበት ኳስ በስተቀር ይሄ ነው የሚባል ሙኩራንም ሆነ ግብ ሳያስመለክቱን ጨዋታው በመቻል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

