በ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ የአዳማ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በሽመልስ በቀለ ግሩም ግብ መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 በማሸነፍ ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት አጥብቧል

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በጨዋታው ጅማሮ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ መቐለዎች ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው አሸናፊ ሐፍቱ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቦና ዓሊ በግራ እግሩ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው የዘለቁት ሐይቆቹ 34ኛው እና 39ኛው ደቂቃ ላይ በምንተስኖት ቶማስ አማካኝነት ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ምዓም አናብስት 51ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ፍጹም ዓለሙ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው አሸናፊ ሐፍቱ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ብሩክ ታደለ በድንቅ ብቃት ከአፋፍ ላይ መልሶበታል።
ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እየተመለሱ የመጡት ሀዋሳዎች 75ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው አድናን ረሻድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሽመልስ በቀለ አስደናቂ በሆነ ክህሎት ከጠባብ አንግል አክርሮ በመምታት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
መቐለዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም ንጹሕ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሐይቆቹ ነጥባቸውን 40 በማድረስ ከመሪው ሲዳማ ያላቸውን ልዩነት ወደ ሁለት አጥብበዋል።

