ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋ ከተማ ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋ ከተማ ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር የ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቐለ 70 እንደርታን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማ ሽረ ምድረ ገነትን 1 ለ 0 ረቷል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቐለ 70 እንደርታ ያገናኘው በሀዋሳ ከተማ የተካሄደ ቀዳሚ  ጨዋታ ግብ ያስተናገደው ገና በሁለተኛው ደቂቃ ሲሆን ሁዘይፋ ሻፊ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ከናትናኤል ዳንኤል የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ጎልነት የቀየራት ኳስም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በያዙበት አጋማሽ ላይ ቦና ዓሊ ከግራ መስመር አሻግሯት ከግቡ አፋፍ የነበረው ብርሃኑ አዳሙ ወደ ግብነት ያልቀየራት ዕድል መቐለ 70 እንደርታን አቻ ለማድረግ የተቃረበች አጋጣሚ ስትሆን ብሩክ ብፁአምላክ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራም የኢትዮጵያ  ንግድ ባንክን መሪነት ከፍ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።
የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎችም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አዲስ ግደይ ከመአዝን አሻምቷት ናትናኤል ዳንኤል
በግምባሩ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት ሙከራም የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራ ስትሆን በ56ኛው ደቂቃም ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁዘይፋ ሻፊ በግሩም መንገድ  ከቀኝ መስመር አሻግራት ናትናኤል ዳንኤል ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ችለዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር አሻምቷት አብዱለጢፍ ባምባ በግምባሩ ከገጫት በኋላ ግብ ጠባቂው ጊቢ ጆቤ ያዳናት እንዲሁም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ አሻግሯት አይባሚ ፕሪንስ ያመከናት አጋጣሚ በመቐለ 70 እንደርታ በኩል የተደረጉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ሲሆኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ሁዘይፋ ሻፊ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አዲስ ግደይ ያደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ እና ዳዊት ዮሐንስ የግብ ጠባቂው መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ የሞከረው ኳስ የቡድኑን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ። በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ጨዋታም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሽረ ምድረ ገነት ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሽረ ምድረ ገነት ከ ድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር።

ድሬዳዋ ከተማዎች በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ጀሚል ያዕቆብ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ እንዲሁም መሐመድኑር ናስር ከአስራት ቱንጆ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ መቶት ተቀይሮ የገባው ሬችሞንድ አይ ያዳነው ለግብ የቀረበ ሙከራም የሚጠቀሱ የግብ አጋጣሚዎች ናቸው። የመጀመሪው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩትም መሐመድኑር ናስር የሽረ ምድረ ገነት ተጫዋቾች በራሳቸው ሳጥን በሰሩት የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር ብርቱካናማዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት እንዲሁም ቡድኖች በተሻለ የማጥቃት አጨዋወት የቀረቡበት ሲሆን በሽረ ምድረ ገነት በኩል ዳንኤል ዳርጌ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ያገኛትን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ በመምታት ሞክሯት ፍሬው ጌታሁን በድንቅ ብቃት ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራም ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረበች የአጋማሹ ቀዳሚ ለግብ የቀረበች አጋጣሚ ነች።

በብርቱካናማዎቹ በኩልም አብዱሰላም የሱፍ በረዥሙ አሻግሯት መሐመድኑር ናስር በግምባሩ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም አስራት ቱንጆ በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ደርሳ ጀሚል ያዕቆብ ያመቻቻትን ኳስ መቶ ክፍሎም ገብረህይወት ከግቡ መስመር የመለሳት የድሬዳዋ ከተማን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች። ተቀይሮ የገባው ሄኖክ ተወልደ ግብ ጠባቂው ሬችሞንድ አይ በረዥሙ ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራም በመጨረሻው ደቂቃ ሽረ ምድረ ገነትን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ስትሆን በሁለተኛው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም በድሬዳዋ ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።