ሪፖርት | ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት | ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ድል ቀንቷቸዋል

ዐፄዎቹ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ሲታረቁ የጦና ንቦቹ በጭማሪ ደቂቃ ባገኙት ግብ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በከባድ ዝናባማ አየር በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተን ሲሆን 9ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳው ያሬድ ብሩክ ሞክሮ ግብ ጠባቂው በመለሰበት፣ እንዲሁም 22ኛው ደቂቃ ላይ፣ የፋሲል ከነማው ታምራት ኢያሱ ወደ ግብ መቶት ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በጥሩ ቅልጥፍና በመለሰበት ሙከራ ለግብ መቅረብ ችሎ ነበር።

23ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማው ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ ላይ እንዲሁም 35ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ አብዱልአዚዝ አማን በግንባሩ ገጭቶ የሞከሩትን ኳስ  ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል። 38ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ቃልኪዳን ዘላለም በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ሙከራ የግብን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ይህም ለፋሲል ከነማ እጅግ አስቆጪ ሙከራ ነበር::

ከእረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ፋሲል ከነማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 67ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ኪሩቤል ዳኘ ያሻገረውን ኳስ ምኞት ደበበ በግንባሩ በመግጨት ዐፄዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ውሃ በቋጠረው እና ኳስ በመሬት  ለማንሸራሸር ምቹ ባልነበረው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ የመጨረሻዎችን ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች በተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርጉም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። በተቃራኒው ፋሲል ከነማዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ በምኞት ደበበ ሃፍ ቮሊ ግሩም ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በሚገርም ንቃት ግብ እንዳይሆን አድርጎታል። ጨዋታውንም ዐፄዎቹ 1-0 ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ወላይታ ድቻ

በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው ውሃ በማቋጠሩ ምክንያት ሁለቱም ቡድኖች የሚፈልጉትን ጨዋታ ለመጫወት ሲቸገር ተስተውሏል። በአጋማሹም 14ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች በካርሎስ ዳምጠው የግንባር ኳስ አማካኝነት ለግብ መቅረብ የቻሉ ቢሆንም ነገር ግን በግቡ ቋሚ ወጥቶባቸዋል። በጥሩ ቅብብሎች ግብ ለማግኘት ጥረት ሚያደርጉት ወልዋሎዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ ከቅጣት ምት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ካዲሚ ዲያዬ እንደምንም ብሎ በእግሩ መቶ በግብ አግዳሚ በኩል እንዲወጣ አድርጎታል።

ከእረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን 66ኛው ደቂቃ ላይ ቀይረው ባስገቧቸው አቤኔዘር አለማየሁ እና ያሬድ ዳርዛ አማካኝነት በተከታታይ ወደ ግብ የሞከሩት ሙከራ በግብ ጠባቂው ሙታክብዋ ጆኤል ተደጋጋሚ ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል።

90ኛው ደቂቃ ላይ በቸርነቱ ኡፋይሳ የግንባር ኳስ አስደናቂ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ወላይታ ዲቻዎች ከአንድ ደቂቃ 90+1 ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው መሳይ ሰለሞን ወደ ግብነት ቀይሮ የማታ ማታ የጦና ንቦችን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።