ሪፖርት| በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄዱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

ሪፖርት| በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄዱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

በአዲስ አበባ በተካሄዱ የ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ሸገር ከተማና ነጌሌ አርሲ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

ሸገር ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ

ቀዝቃዛ በነበረው አጋማሽ የነጌሌ አርሲዎቹ ዳዊት ተፈራ እና ሀቢብ ከማል 28ኛ እና 29ኛ ደቂቃ ላይ አከታትለው ካደረጓቸው ዒላማቸውን የጠበቁ ግን ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራዎች እና ከቤ ብዙነህ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ማራኪ በሆነ ፉክክር ቀጥሎ 51ኛው ደቂቃ ላይ የሸገሩ ቢኒያም ፍቅሩ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ አስወጥቶበታል።

ጨዋታው 60ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስም ሰጎኖቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከረጅም ርቀት ተመትቶ አግዳሚውን ገጭቶ የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ከቤ ብዙነህ በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን ተቆጣጥሮ በተከላካዮች መካከል ሆኖ በመምታት በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።

ሸገሮች መመራት በጀመሩበት ቅጽበት ፈጣን ምላሽ በመስጠት 64ኛ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሮሆቦት ሰላሎ ቡልቻ ሹራ ላይ ጥፋት ሠርቷል በሚል የተሰጠውን የቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ በድንቅ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ ነጌሌዎች 81ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ከቤ ብዙነህ የቀነሰለትን ኳስ ያገኘው ምስጋናው መላኩ መሬት ለመሬት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ አስወጥቶበታል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ተጨምረው የሸገሩ ተከላካይ አቤል አየለ የነጌሌው ናትናኤል ሰለሞን ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ሮሆቦት ሰላሎ 90+7 ላይ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ እና የግቡ የላይ አግዳሚ  ግብ ከመሆን አስቀርተውታል፤ ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የፈረሰኞቹ ብልጫ በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ ፉክክር ሲደረግ 28ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጩ ጄሮም ፊሊፕ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ሙከራ አድርጎ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ከወጣበት በኋላ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሀብታሙ ጉልላት ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን በጥሩ ዝላይ በግንባር በመግጨት ግብ አድርጎታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተሻለ መነሳሳት ጨዋታውን ያስቀጠሉት ፈረሰኞቹ 36ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ግብ አግኝተዋል። በማራኪ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ አዲሰ አቱላ ለፍጹም ጥላሁን ሰጥቶት ፍጹም በድንቅ ሁኔታ የሰነጠቀለትን ኳስ በጥሩ ሩጫ ያመቻቸው ተገኑ ተሾመ ግሩም በሆነ የተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮታል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረታቸውን የቀጠሉት አዞዎቹ 42ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። አርባምንጮች ከማዕዘን ኳስ ሲጀምሩ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች በተዘናጉበት ቅጽበት ተሻምቶ ጄሮም ፊሊፕ በግንባር በመግጨት ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ፈረሰኞቹ 47ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ፀጋ ከድር በግሩም ዕይታ የሰነጠቀለትን ኳስ ያገኘው አዲሱ አቱላ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኢድሪሳ ኦጎዶጆ አግዶበታል።

የጊዮርጊሱ ፍጹም ጥላሁን 56ኛ ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከረጅም ርቀት ካደረገው ሙከራ በኋላ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ሙከራ ያላስመለከተን ጨዋታ 89ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስመለክተን ተቃርቦ ሄኖክ ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ያደረገውን ድንቅ ሙከራ ግብ ጠባቂው ወደኋላ ተመልሶ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

ድራማዊ ትዕይንት በነበረባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ባልተረጋጉበት ቅጽበት አርባምንጮች ኳሱን ጀምረውት በስተመጨረሻም ኤፍሬም ታምራት ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ማማዱ ሴክ ኳሱን በግንባር በመግጨት ግብ አድርጎታል። ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።