ሲዳማ ቡናዎች በአቤል ያለው ሁለት ግቦች ድሬዳዋ ከተማን ሲያሸንፉ መቻል እና ሀዋሳ ከተማ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ
ጨዋታው በበርካታ ደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ታጅቦ የተጀመረ ሲሆን ገና በመጀመሪያዎቹ ሰከንዶች የድሬዳዋው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን የሰራውን ስህተት ተከትሎ አቤል ያለው አደገኛ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ስህተቱን በማረም ቡድኑን ታድጓል። ሲዳማ ቡናዎች ከተጋጣሚ ሜዳ ጀምሮ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የድሬዳዋን የኳስ ቅብብል ለመገደብ ያደረጉት ጥረት በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የበላይነትን እንዲይዙ አስችሏቸዋል በተለይም በዮሴፍ ዮሐንስ እና በሬድዋን ናስር አማካኝነት ወደ ግብ ለመድረስ ያደረጓቸው ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

የሲዳማ ቡና የጨዋታ ብልጫ ፍሬ ያፈራው ከ72ኛው ደቂቃ ጥበቃ በኋላ ነበር። ፍራኦል መንግስቱ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አቤል ያለው በግሩም የግንባር ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ስታዲየሙ ውስጥ የሚገኙ ደጋፊዎችን በደስታ አናውጧል። ግቧ ከተቆጠረች በኋላም ሲዳማዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር እና የድሬዳዋን መልሶ ማጥቃት በመከላከል ረገድ የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ሲያመራ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የድሬዳዋው ግብ ጠባቂ አቤል ያለው ላይ በፈጸመው ጥፋት ምክንያት ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ አቤል ያለው ኳስ እና መረብን በማገናኘት የራሱን እና የቡድኑን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ድሉን አረጋግጧል። በዚሁ ቅፅበት የድሬዳዋው ሬድዋን ሸረፋ ከዳኛ ጋር በፈጠረው አላስፈላጊ እሰጣ አገባ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ (ቀይ) ከሜዳ የተሰናበተ ሲሆን ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መቻል ከ ሀዋሳ ከተማ
በሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው እና መቻልን ከ ሀዋሳ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተሞች ብልጫ በመውሰድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችለዋል። የተቀሩትን ደቂቃዎች ወደ ጨዋታ የተመለሱት መቻሎች በፈጣን መስመር አጥቂዎቻቸው ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ነገር ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይሄ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳንመለከት አጋማሹ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በፈጣን ሽግግሮች የታጀበ የግብ ፍላጎት የታየበት ቢሆንም፣ በ83ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው እስራኤል እሸቱ ከቢንያም በላይ ተቀብሎ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራ ብቸኛው አደገኛ አጋጣሚ ነበር። በዚህም ምክንያት ጨዋታው ይሄ ነው የሚባል ተጨማሪ የግብ ዕድል ሳይፈጠርበት ያለምንም ግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

