ሪፖርት | መሪው ሲዳማ ቡና ሽንፈት አስተናግዷል

ሪፖርት | መሪው ሲዳማ ቡና ሽንፈት አስተናግዷል

ኢትዮጵያ መድኖች ሳሙኤል ሳሊሶ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ከወራጅ ቀጠናው የራቁበትን ድል አስመዝግበዋል።

በበርካታ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ደማቅ ድጋፍ የታጀበው ይህ ተጠባቂ ፍልሚያ በመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ መድኖች የበላይነት የታየበት ነበር። መድኖች የተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግቶ የግብ አደጋዎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በተለይም በአልፍሬድ ንኩሩንዚዛ እና በቤንጃሚን ኮቴ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ መድኖችን ለመሪነት እጅግ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም በአጋማሹ ሳይሳካላቸው ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ብልጫውን በመውሰድ በቁጥር በዝተው ወደ ፊት ተጭነው ቢጫወቱም ኢትዮጵያ መድኖች በመልሶ ማጥቃት ባገኙት አጋጣሚ ድል ቀንቷቸዋል። በ82ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ ከግራ መስመር በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ ጥሩ በሆነ በመጀመሪያ ኳስ ንክኪ የቀድሞ ቡድኑ ላይ ግብ አስቆጥሮ መድኖችን መሪ አድርጓል።

በጭማሪ ደቂቃ የሲዳማው ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ መልሶበታል። ጨዋታውም በመድን 1 ለ 0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ርቆ ፋታ የሚያገኝበትን ወሳኝ ውጤት ሲመዘግብ ሲዳማ ቡና ደግሞ ነጥቡን አሳድጎ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያሰፋበት ዕድሉን አጥቷል።