ፈረሰኞቹ የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል

ፈረሰኞቹ የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስቡን ለማጠናከር ተጫዋቾች ማስመጣቱን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

ከሜዳ ውጪ ባሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲፈተን የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮ የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ31 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ 39 ነጥቦችን በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ይታወቃል። ክለቡ ያለበትን የፋይናንስ ውስንነት ከሰሞኑን ካስተካከለ በኋላ ተጫዋቾች እንዳያስፈርም እግድ ላይ የወደቀበትን ውሳኔ አስነስቶ በገበያው ነፃ የሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ተጫዋቾችን በመፈለግ ላይ ተጠምዶ የነበረ ሲሆን አሁን አራት የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ማስመጣቱን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

የዝግጅት ክፍላችን ከአራቱ ተጫዋቾች የሁለቱን ማንነት ከመረጃ ምንጮቿ ማግኘት ችላለች። ቡድኑን ዛሬ በይፋ የተቀላቀልል የመጀመሪያው ተጫዋች ጋናዊው ኬልቪን ዶሴ ነው። አንድ ሜትር ከዘጠና ሴንቲሜትር የሚረዝመው ባለግራ እግር የመሐል ተከላካይ ከሀገሩ ክለብ ማውንቴነርስ ጀምሮ እስከ አልባኒያ አንደኛ እና ሁለተኛ ሊጎች የተጫወተ ሲሆን አሁን መዳረሻው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆኗል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የአጥቂ መስመር ተሰላፊው አልፍሬድ ሜንሳህ ነው። አልፍሬድ ሜንሳህ እንደ ቡድን አጋሩ ኬልቪን ዶሴ በአልባኒያ ሊግ የመጫወት ልምድ ያለው ሲሆን ከአልባኒያ በተጨማሪም በኮሶቮው ክለብ ባልካኒ የእግርኳስ ህይወቱን መርቷል።

ሁለቱም ጋናዊያን ኢትዮጵያዊው ተጫዋች ቢኒያም በላይ ከዚህ ቀደም የተጫወተበት የአልባኒያው ስኬንደርቡ ክለብ ተጫውተው አሳልፈዋል።

ከላይ እንደገለፅነው ክለቡ በድምሩ አራት ተጫዋቾችን ከውጪ ያስመጣ ሲሆን ስማቸውን የገለፅናቸውን ጨምሮ ቀሪዎቹ ሁለቱን ዛሬ አመሻሽ በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ለደጋፊዎች ይፋ ለማድረግ ለመገናኛ ብዙሃን ጥሪ አቅርቧል።