መረጃዎች | የ32ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ32ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ፤ የዕለቱን መርሐ ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል !

ሲዳማ ቡና ከ ሀድያ ሆሳዕና

በሀምሳ አምስት ነጥብ ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች አጣብቂኝ ውስጥ የገባው መሪነታቸው ለማፅናት ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሀድያ ሆሳዕናን ይገጥማሉ።

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ተለያይተው በኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ በመደዳ ሽንፈት አስተናግደው ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥብ አንዱን ብቻ ያሳኩት ሲዳማ ቡናዎች በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ተከታዮቻቸው ነጌሌ አርሲ እና መቻል በሚገናኙበት የጨዋታ ሳምንት ድል አድርገው ብያንስ ከአንዳቸው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ድል ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስም ባለፉት ሦስት መርሐ ግብሮች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለውን የፊት መስመሩ ማሻሻል ይኖርበታል።

በሰላሣ ስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ከሊጉ መሪ ጋር ይፋለማሉ።

በመጨረሻው መርሐ ግብር ከአራት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሀዋሳ ከተማን አንድ ለባዶ በመርታት ሙሉ ነጥብ ያሳኩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የዛሬው ጨዋታ በወራጅ ቀጠናው ጫፍ ላይ ካለው
ድሬዳዋ ከተማ በአራት ነጥብ ርቀት ላይ ሆነው የሚያከናውኑት እንደመሆኑ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።
በዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም ባለፉት አራት መርሐ ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለውን የፊት መስመሩን አሻሽሎ ጠንካራውን የተጋጣሚው የተከላካይ መስመር መፈተን በሚችልበት አኳኋን መቅረብ ይጠበቅበታል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 13 ጨዋታዎች አድርገዋል። አራት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 20 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና አምስት ፣ 15 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ አራት ድሎችን አስመዝግበዋል።

ሽረ ምድረ ገነት ከ ኢትዮጵያ ቡና

በሰላሣ ሦስት ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ያላቸውን ተስፋ ለማለምለም ከቡናማዎቹ ጋር ይፋለማሉ።

በመጨረሻው መርሐ ግብር በአዳማ ከተማ የአራት ለባዶ አስከፊ ሽንፈት የደረሰው ቡድኑ ወደ ጨዋታው ከስምንት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አንድ ለባዶ አሸንፎ ቢቀርብም የነበሩበት የመከላከል ድክመቶች አራት ለባዶ እንዲሸነፍ አድርጎታል። በቀደመው ውጤታማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ መዝለቅ ያልቻለውና በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ በቀዳሚነት የማጥቃት አጨዋወቱን ማሻሻል ይጠበቅበታል።

በአርባ ሦስት ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ ለመጠጋት የሚያችላቸውን ነጥብ ለማግኘት ሽረ ምድረ ገነትን ይገጥማሉ።

በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ የተጋሩት እና በቅርብ ሳምንታት በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመደዳ ሁለት ድሎች ካሳኩባቸው መርሐ ግብሮች በኋላ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች አምስት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገብ ችለዋል። በተጠቀሱት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርጎ ደረጃውን ለማሻሻል በሚከውነት ጨዋታ በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐ ግብሮች በቀደመ ውጤታማነቱ መዝለቅ ያልቻለውን የፊት መስመር ማሻሻል እንዲሁም መሪነቱን በማስጠበቅ ረገድ ያለውን ድክመት መቅረፍም ከቡድኑ ይጠበቃል።

ሽረ ምድረገነቶች አቤል እንዳለን በጉዳት ሽመክት ጉግሳ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ፀጋአብ ዮሐንስን ደግሞ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 5 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም በእኩሌታ ሁለት ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል።
በጨዋታዎቹ ቡናማዎቹ አራት ግቦች ሲያስቆጥሩ፤ ሽረዎች አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በአርባ አንድ ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች አስደናቂው የማንሰራራት ጉዟቸውን ለማስቀጠል ከፈረሰኞቹ ጋር ይፋለማሉ።

ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት የጦና ንቦች ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ያስገኙላቸው ድሎች በማስመዝገብ ከስጋት ቀጠናው መራቅ ችለዋል። ወላይታ ድቻዎች በፋሲል ከነማ ከተረቱበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው አራት መርሐ ግብሮች ከሽንፈት ከመራቅ ባለፈ ሦስት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን በማሳካት አስደናቂ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በያዙት የድል መንገድ ለመቀጠልም በመጨረሻው ጨዋታ በማጥቃቱ ረገድ የታየው መሻሻል ማስቀጠል እንዲሁም በመከላከሉ በኩል የታዩ ውስን ክፍተቶች ማረም ይጠበቅባቸዋል።

በሰላሣ ዘጠኝ ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከስጋት ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት የጦና ንቦቹን ይገጥማሉ።

በፀጋ ከድር የመጨረሻ ደቂቃ ግብ መቐለ 70 እንደርታን አንድ ለባዶ ረተው ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሱት ፈረሰኞቹ ከወራጅ ቀጠናው ያላቸውን የአራት ነጥብ ርቀት ከፍ አድርገው ደረጃቸው ለማሻሻል ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካለው ቡድን ጋር በሚገኙበት የዛሬው ጨዋታም በአራት መርሐ ግብሮች ሰባት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ኳስና መረብ ያገናኘውን የፊት መስመራቸው ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች 23 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ወላይታ ድቻ ደግሞ 7 ድሎችን ሲያሳኩ አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 ወላይታ ድቻ ደግሞ 18 ጎሎች አስቆጥረዋል።

መቻል ከ ነጌሌ አርሲ

በአርባ ዘጠኝ ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቻል በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በ2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን ነጌሌ አርሲ ይገጥማል።

በ31ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ተለያይተው 2ኛ ደረጃነትን ለሰጎኖቹ  አሳልፈው የሰጡት መቻሎች ከዛሬው ተጋጣሚያቸው ጋር በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ ሆነው በሚደርጉት ፍልሚያ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻሉ የደረጃ መሻሻል ከማግኘት አልፈው በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ያላቸውን ዕድል ከፍ ለማድረግ ያስችላቸዋል። መሪው ሲዳማ ቡና በተከታታይ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በፉክክሩ የተሻለ ተስፋ ያገኙት መቻሎች በመደዳ ነጥብ ከተጋሩባቸው ሁለት ጨዋታዎች መልስ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ባለፉት አምስት መርሐ ግብሮች ውስጥ በሦስቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ወጥቶ ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱን ማሻሻል ይኖርበታል።

ሀምሳ አንድ ነጥብ ሰብስበው ከመሪው ሲዳማ ቡና በአራት ነጥብ ርቀት ላይ በመቀመጥ በ2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ነጌሌ አርሲዎች የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ ወይም ባለበት ለማስቀጠል ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።

አምስት ድል አልባ ሳምንታት ካሳለፉ በኋላ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፈው የመሪው ሲዳማ ቡና ነጥብ መጣል በአግባቡ በመጠቀም ዳግም ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ብቅ ያሉት ሰጎኖቹ ድል ባደረጉባቸው ያለፉት ሁለት መርሐ ግብሮች ያሳዩትን ብቃት ማስቀጠል ቀዳሚ ስራቸው ነው። በተለይም ከረዥም ጊዝያት በኋላ ዳግም ወደ ውጤታማነቱ የተመለሰውና በሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸውን ብቃት ማስቀጠል ከቡድኑ የሚጠበቅ ሲሆን ከጠንካራው የመቻል የተከላካይ ክፍል የሚያደርጉት ፍልሚያም የጨዋታውን ውጤት ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ነጌሌ አርሲዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ በነጌሌ አርሲ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።