ሪፖርት | ሲዳማ ቡና መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል ሲቀዳጅ መቐለ እና ባህር ዳር አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ሲዳማ ቡና መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል ሲቀዳጅ መቐለ እና ባህር ዳር አቻ ተለያይተዋል

ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን 1ለዐ በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያሳካ መቐለ 70 እንደርታ እና ባህርዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።

ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ

በሲዳማ ቡና የጨዋታ የበላይነት ጅማሮውን ያደረገው ተጠባቂው ጨዋታ የአዳማዎችን ደካማ እንቅሰቃሴ ባደረጉባቸው በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች በኋላ ግብ ተቆጥሮበታል። በተደጋጋሚ እየገቡ የአዳማን ተከላካይ ሲፈትኑ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ያሬድ ባዬ ወደ ግብ ሲመታው ተጨራርፎ እያወጣ ያለውን ኳስ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ ካደረጋቸው ከሁለት ደቂቃ ላዩነት ብርሃኑ በቀለ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ ያደረገው ሙከራ ግብ ጠባቂው እንዴትም ባያወጣባቸው መሪነታቸውን ለማጠናከር የቀረቡበት አደገኛው ሙከራ ይጠቀሳል።

ከግቡ በኋላ የተነቃቁት አዳማዎች ኳስ ይዘው ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም የሲዳማ ቡናዎች የተከላካይ መስመር አደረጃጀት ኳሶችን እያቋረጠባቸው ተቸግረው በአንድ አጋጣሚ አደገኛ ሙከራ በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ አድርገው የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባቸው አጋማሹ ተገባዶ ለዕረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ የመጀመሪያ አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃዎች ባሳዩት ጥንካሬ ይበልጡን ተጠናክሮ የተመለሱት አዳማዎች ጫን ብለው እየገቡ የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ በሙሉ ኃይላቸው እየገቡ ያደረጉ ሲሆን በመከላከሉ የማይታማው የሲዳማ ቡና ተከላካይ መስመር ወደ እጁ የገባውን ሶስት ነጥብ አስጠብቆ ለመውጣት ወደ ኋላ አፈግፍጎ በመጫወቱ አስቆጪ አጋጣሚ ከመፍጠር የዘለለ ግብ ማግኘት ተስኗቸዋል።

ጠባቡን የግብ ልዩነት አስጠብቀው ለመውጣት መልሶ ማጥቃቱን ብቻ ምርጫቸው ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች አልፎ አልፎ ወደፊት እየገቡ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ሦስት ነጥብ አስገኝቶላቸው ለመጠናቀቀ ተገዷል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ባህርዳር ከተማ

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተደረገው ምዕም አናብስቶችን ከጣና ሞገዶች ያገናኘው ሁለተኛው ጨዋታ በፈጣን ሽግግር ማራኪ እንቅስቃሴ ለተመልካች እያስመለከተ ጅማሮውን ሲያደርግ ግብ ለማግኘት በአጫጭር ቅብብል ሲገቡ የነበሩት መቐለዎች በአጋማሹ አደገኛ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ ነበሩ፤ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ስምዖን ማሩ ያደረገው ጠንካራው ሙከራ እና 20ኛው ደቂቃ ላይ ቦና አሊ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ የተሻረባቸው እንዲሁም በቆመ ኳስ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ አድርጎት ፔፔ ሴይዶ የተቆጣጠረባቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሾች ነበሩ።

በኳስ ቁጥጥር ደካማ ባይሆኑም ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ክፍል ሲደርሱ እምብዛም ያልታዩት የጣና ሞገዶች ወንደሰን በለጠ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ በፍጥነት ደርኮ የመታው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት ያለፈበት እና መጠናቀቂያው ላይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ አንተነህ ተፈራ ብቻውን ሆኖ መቆጣጠር ተስኖት ያመለጠው አስቆጪው አጋጣሚ ሲጠቀስ አጋማሹም ያለግብ ተገባዷል።

በተመጣጣኝ ጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለሰው በሁለተኛ አጋማሽ የጣና ሞገዶች በሙከራዎች ጋር የተመለሱ ሲሆን ፍቅርሚካኤል ከሳጥን ውጪ ሆኖ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ሶፎንያስ ያዳነበት እንዲሁም የጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ወንደሰን በለጠ በራሱ ጥረት ገብቶ ከግብ ጠባቂው ፈትለፊት ሆኖ ጠንከር ያለ ሙከራ ሳያደርግ ቀርቶ ሶፎንያስ የተቆጣጠረባቸው አስቆጪው አጋጣሚ ይታወሳል።

ከእረፍት መልስ አንፃራዊ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ምዓም አናብስት በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ጥረት ያድርጉ እንጂ የጠራ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።