ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ35ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ35ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

በሀገራት የወዳጅነት ጨዋታ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ጅማሮን ሲያደርግ እነሱን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና

በደረጃ ሰንጠረዡ በ46 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በዛሬው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስና ደረጃውን ለማሻሻል ይጫወታል። ቡድኑ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎቹ 1 ድል፣ 2 አቻ እና 2 ሽንፈት ያስመዘገበ ሲሆን 36 ግቦችን አስቆጥሮ 37 ግቦችን ማስተናገዱ ቡድኑ የ-1 የግብ ዕዳ ባለቤት እንዲሆን አድርጎታል ። ይህ በቀላሉ ግብ የመፍቀድ ሁኔታ የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ሆኖ የቆየ ቢሆንም እንደ ፋሲል ከነማ ያሉ ጠንካራ ክለቦችን 2 ለ 1 ያሸነፈበት የማጥቃት መስመር ብቃቱ ግን ሊናቅ የማይችል ጥንካሬው ነው። ኢትዮጵያ ቡና በመሃል ሜዳ ላይ ብልጫን በመውሰድ የሲዳማ ቡናን ኳሶች ማቋረጥና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልትን መተግበር ከቻሉ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው የመውጣት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

በ34 ጨዋታዎች 61 ነጥቦችን ሰብስቦ የሊጉ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ 3 ሽንፈቶች አስተናግዶ ራሱን አጣብቂኝ ውስጥ ቢከትም በመጨረሻዎቹ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በድል ታጅቦ ወደ አሸናፊነት ቦታው ተመልሷል። የቡድኑ አስፈሪነት የሚጀምረው 39 ግቦችን አስቆጥሮ 20 ግቦችን ብቻ ካስተናገደውና የ+19 ንጹህ የግብ ክፍያ ካስገኘለት ጠንካራው የተከላካይ አጥሩ ሲሆን ይህ የአጥር ጥንካሬው የዛሬውም ትልቅ መተማመኛው ነው። አልፎ አልፎ የሚታይበትና ዋጋ የሚያስከፍለው የትኩረት ማጣት ደካማ ጎኑ ቢሆንም የዛሬውን ወሳኝ ፍልሚያ አሸንፎ መሪነቱን ይበልጥ ለማጠናከር የአሸናፊነት ስነ-ልቦናውን ይዞ መግባት እንዲሁም የመሃል ሜዳውን የበላይነት መቆጣጠር እና የኢትዮጵያ ቡናን የኋላ ክፍል በፈጣን አጥቂዎቹ ያለ እረፍት መጫን ይኖርበታል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 31 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡናዎች 11 ጊዜ ድል ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ቡናዎች 10  ጨዋታዎችን አሸንፈዋል። 10 ጊዜ አቻ  ደግሞ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 37 ሲዳማ ቡና 34 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቻል

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ46 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና የደረጃ ማሻሻያ ለማድረግ ዛሬ ወደ ሜዳ ይገባል። ቡድኑ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት፣ በሁለቱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ በመለያየት በጥሩ መነሳሳት ላይ ሲሆን በተለይም በቅርብ ሳምንታት ድሬዳዋን ሁለት ለአንድ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማን አንድ ለባዶ ያሸነፈበት ውጤት ለዛሬው ጨዋታ ተጨማሪ መነሳሳትን ይፈጥርለታል። በ34 ጨዋታዎች 28 ጎሎችን አስቆጥሮ 30 ጎሎች ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመሩን ማጠናከር የሚችል ከሆነ የዛሬውን ተጠባቂ ጨዋታ በበላይነት ማጠናቀቅ የሚችልበትን እድል መፍጠር ይችላል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ53 ነጥብና በ17 የጎል ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቻል ከሲዳማ ቡና እና ከነገሌ አርሲ ጋር ለዋንጫ ብርቱ ፍክክር ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በውድድሩ መጠናቀቂያ ሳምንቶች ላይ ባሳየው መንሸራተት ከመሪው ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት እየሰፋ ሄዷል። በቁጥራዊ ስሌት ሲታይ አሁንም ሙሉ በሙሉ ከዋንጫ ፉክክር ውጪ ባይሆንም አሁን ላይ ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቦ ወደ ዋንጫው ለመድረስ የዛሬውን እና ቀሪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የግድ ይሆንበታል ። በሊጉ የ 43 ግቦች ባለቤት የሆነው ጠንካራው የፊት መስመሩ ዛሬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለሚያደርገው ፍልሚያ ያላቸውን ልምድ እና ችሎታ ተጠቅመው ቡድኑን ወደ አሸናፊነት እንደሚመልሱ ይጠበቃል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ብርሃኑ አሻሞ በቅጣት ምክንያት የማይኖር ሲሆን በመቻል በኩል ኮሊንስ ኮፊ በጉዳት ፣ ፈቱዲን ጀማል ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይኖርም።

ኢትዮጵያ መድን ከ ድሬዳዋ ከተማ

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ43 ነጥብና በ3 የጎል ክፍያ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የውጤት ጉዞ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ተከታታይ ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ላይ ምንም አይነት ሽንፈት ያላስተናገደ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎቹ ደግሞ በሁለቱ ድል ቀንቶት በሶስቱ አቻ በመለያየት አስተማማኝ አቋም አሳይቷል። በ34 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን አስቆጥሮ 26 ጎሎችን ያስተናገደው መድን ይህንን ያልተሸነፈበትን ግስጋሴ አስጠብቆ በመጓዝ የደረጃ ሰንጠረዡን ይበልጥ ለማሻሻል የሚያስችለውን ቁመና ይዟል። የዛሬው ጨዋታም ቡድኑ ይዞት የመጣውን ተከታታይ የአሸናፊነት ጉዞ የሚቀጥልበት ወይስ በተቃራኒው ጠንካራ ፈተና ይገጥመዋል? የሚለው የሚታይበት ይሆናል።

በተቃራኒው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ35 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ በአሁኑ ሰዓት እጅግ ፈታኝ በሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ተከታታይ ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ድል ማድረግ ያልቻለ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎቹም ማግኘት የቻለው ሁለት ነጥብ ብቻ ነው። በተለይም ድሬዳዋ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ምድረገነት ሽረን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ ጀምሮ ላለፉት 67 ቀናት ሙሉ ከድል ርቆ መቆየቱ የቡድኑን ወቅታዊ ፈተና ያሳያል። የሊጉ መጠናቀቂያ ሳምንታት በጣም ጥቂት መሆናቸውን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትና በሊጉ ለመቆየት የዛሬው ጨዋታ ለድሬዳዋ ከተማ እጅግ ወሳኝና የነጥብ ማግኛ አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ተከላካዩ በረከት ካሌብ እና ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በድሬዳዋ በኩል የቡድን ዜና ማግኘት አልቻልንም።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ ተገናኝተው መድን 5 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናው ድሬዳዋ ከተማ 3 ጨዋታዎች አሸንፏል፤ የተቀሩት 3 ግንኙነቶች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተደመደሙ ነበሩ።  በጨዋታዎቹ መድን 16 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።