በዛሬው ዕለት አመሻሽ ላይ በይፋ በሸራተን አዲስ ሆቴል ለመጪዎቹ ዓመታት የፈረሰኞቹ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሰርቢያዊው ሰርዶቪች ሚሉቲን ሚቾ ከትውውቃቸው በኋላ ተከታዩን ሀሳብ አንስተዋል። 
“ምንም እንኳን የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውልኝ የነበረ ቢሆንም ውስጤን በማዳመጥ ወደዚህ መጥቻለሁ። አላማችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ቀደመው ስፍራው መመለስ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ከምርጦቹ ተርታ መሰለፍ ነው።”
“ለዚህም የአምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅዶች አሉን ፤ በመጀመሪያው ዓመት የሊጉንና የኢትዮጵያ ዋንጫን ማሸነፍ በቀጣይ አምስት አመታት ደግሞ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ቤተኛ ከመሆን ባለፈ በ2030 ኢትዮጵያን ለዓለም ዋንጫ የማብቃት ውጥን ይዘናል።”
“የአሰልጣኝ ቡድናችንን ለማጠናከር የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ከቤልጂየም የአካል ብቃት አሰልጣኝ ከፔዤ እና ፊዚዮ ከውጭ ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን።”
“ባደረግናቸው ዝውውሮች ውስጥ በጣም ለመጠንቀቅ ሞክረናል ፤ ከአንድ ተጫዋች በስተቀር ሁሉም ተጫዋቾቻችን ከ25 ዓመት በታች ናቸው ፤ አሚኑ ካለው ልምድ እና ስነምግባር መነሻነት ልምድ የሚያስፈልገው የተከላካይ መስመራችን እንዲረዳ እኛ ጋር አቆይተነዋል።”
“ከቀጣይ ሳምንት አነስቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እንጀምራለን በዚህም በተለበይ በመጀመሪያዎቹ 3 ሳምንታት በቀን አራት ጊዜ ጠንካራ ልምምዶችን እንሰራለን ፤ ከኢትዮጵያ አዲስ አመት በኋላ በምስራቅ አፍሪካ በተመረጠ ሀገር ዝግጅታችንን እንቀጥላለን ፤ በዚህም ሁለት ወይም ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን የማድረግ ዕቅድ አለን ምክንያቱም አንድ የውጭ የወዳጅነት ጨዋታ አምስት የሀገር ውስጥ ጨዋታዎች ይበልጣል።”

