የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ነገሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድል ቀን አሳልፈዋል።
በዐቢዩ አረጋሽ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 ሀላባ ከተማ
9:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ብልጫ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ወደ ግብ የሚቀየር ውጤታማ ሙከራ ሳያደርግ ተጠናቋል። ሀላባ ከተማም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የኳስ ቁጥጥሩንና የማጥቃት ጥረቱን በማሳደግ የተሻለ ቡድን ሆኖ ቀጥሏል። በ55ኛው ደቂቃ በተቀያሪነት ወደ ሜዳ የገባው ካሌብ ስቲፍ ከአብዱልመጂድ ሁሴን የተቀበለውን ኳስ በግራ እግሩ ወደ ግብነት በመቀየር ኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጓል።
ግቡ ከተቆጠረባቸው በኋላ ሀላባ ከተማዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል ቢሞክሩም የነበራቸውን ጥረት ወደ አቻ ውጤት መቀየር አልቻሉም። በመጨረሻም ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 በማሸነፍ ሦስት ነጥቦችን አሳክቷል።
ነገሌ አርሲ 1-0 ጋሞ ጨንቻ
10:00 ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጋሞ ጨንቻን የገጠመው ነገሌ አርሲ በጨዋታው አብዛኛው ክፍለ ጊዜ የተሻለ ብልጫ በማሳየት የ1ለ0 ድል አስመዝግቧል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርና በግብ ሙከራዎች የተሻለ የነበረው ነገሌ አርሲ በ24ኛው ደቂቃ መሐመድኑር ናስር በተቃራኒው ቡድን የግብ ክልል ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ጋሞ ጨንቻ በአጋማሹ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ሳያደርግ ዕረፍት ወጥቷል።
በሁለተኛው አጋማሽም ነገሌ አርሲ የኳስ ቁጥጥሩን በመቆጣጠርና በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ግልጽ ብልጫውን አስቀጥሏል። ጋሞ ጨንቻ ውጤቱን ለመቀየር ቢጥርም የነገሌ አርሲን መከላከል ማለፍ አልቻለም።
በዚህም ነገሌ አርሲ 1ለ0 በማሸነፍ አራተኛ ተከታታይ የሊግ ሽንፈቱን ለጋሞ ጨንቻ አስመዝግቦበታል። ነገሌ አርሲ በድሉ ምክንያት የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መሪነት ይዟል።

ፋሲል ከነማ 0-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
10:00 ላይ በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም የተደረገው የፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ1ለ0 ድል ተጠናቋል።
በጨዋታው 36ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሪነት ግብ አስቆጥሯል። ብሩክ ብፁአምላክ ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ ኢዮብ ተስፋዬ ወደ ግብ በመምታት ሞክሮ የፋሲል ከነማ ተከላካይ ፍሬዘር ኳሳ ከመለሰው በኋላ አናንያ ጌታቸው በድጋሚ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ሁዘይፋ ሻፊ ኳሱን በመጨረሻ ንክኪ ወደ ግብነት በመቀየር ባንክን መሪ አድርጓል። ይህ ግብ ሲቆጠር የመጨረሻው ንክኪ ከጨዋታው ውጪ ነው በሚል እና የመጀመሪያው ፍሬዘር የመለሰው ኳስ በእጅ የተመለሰ ነው በሚሉ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ከፍተኛ ክርክር ተነስቶ አራቱም ዳኞች ለ6 ደቂቃዎች ያህል ጨዋታው ከተቋረጠ በኋላ በስተመጨረሻም ጎሉን አፅድቀውታል። የመጀመሪያው አጋማሽም በንግድ ባንክ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ፋሲል ከነማ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቢመስልም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደራጀ የመከላከል አቀራረብና በአጋጣሚዎች ላይ በተሻለ የግብ ሙከራ ውጤታማ ሆኗል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጨዋታውን ውጤት ለማስፋት የፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ ሄኖክ ኤርምያስ ያደረገው ሙከራ በፋሲል ከነማ ግብ ጠባቂ ሞኢስ ፖዎቲ ተመልሷል። ሆኖም ይህ ባንኩ ያገኘውን የ1ለ0 ድል ከማስጠበቅ አላገደውም።

