ዩጋንዳዊው የቀድሞ የሲዳማ ቡና የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የተጣለበት የእግድ ውሳኔን በተመለከተ አዲስ መረጃ ወጥቷል።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሎ የነበረው ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካልዬዋ በመጀመሪያ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው ጥሩ የሚባል ጊዜን በማሳለፍ 17 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ (1528 ደቂቃዎች) ለቡድኑ መልካም የሚባል ግልጋሎት ሲሰጥ ማሳለፉ ይታወሳል። ከወራት በፊትም የግብ ዘቡ በሀገሩ በጨዋታ ማጭበርበር ተጠርጥሮ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝና የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚወጣ ለጊዜው ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ እንደታገደ ተገልፆ ነበር። ዛሬ በተሰማ መረጃ ደግሞ የግብ ዘቡን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ ተሳትፈዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መወሰኑን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዩጋንዳ እግር ኳስ ማኅበር የሥነ ምግባር እና ዲሲፕሊን ኮሚቴ ዲሴምበር 21 2024 በተደረገው የኪታራ እና የኤክስፕረስ ጨዋታ ላይ በተፈጸመ የውጤት ማጭበርበር ድርጊት ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ ተጫዋቾች እና የቀድሞ የክለብ ኃላፊዎች ላይ ከባድ የእገዳ ውሳኔ ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል። ኮሚቴው በመስከረም ወር በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ባደረጋቸው ስብሰባዎች የምርመራ ክፍሉን የመጨረሻ ሪፖርት፣ የቀረቡ የጽሑፍ መከላከያዎችን እና የቃል ችሎቶችን በዝርዝር መርምሮ ውሳኔውን አስታውቋል።
በውሳኔው መሠረት የቀድሞ የኤክስፕረስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ሚሮ አሽራፍ ለውርርድ ዓላማ ሲባል ሦስት ጨዋታዎችን ለማጭበርበር በማቀድና በመሳተፍ ጥፋተኛ በመባላቸው ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በዕድሜ ልክ ታግደዋል። ሚሮ አሽራፍ በኪታራ እና ኤክስፕረስ ጨዋታ ላይ የቀረበላቸውን ገንዘብ ተቀብለው ማጭበርበሩን ከመፍቀዳቸውም በላይ ሙትያባ ሃሰን ከተባለ ዩጋንዳዊ እና ጌኖ ከተባለ በእስያ ከሚገኝ የውርርድ አቀናባሪ ጋር በመመሳጠር የኤክስፕረስ እና የዩፒዲኤፍ ጨዋታ ውጤትን ለማስቀየር ተስማምተው ነበር። በተጨማሪም በብዋይስ በሚገኝ ሆቴል ከተጫዋቾች ጋር ስብሰባ በማዘጋጀት የኢንቴቤ ዩፒፒሲ እና የኤክስፕረስ ጨዋታን ለማጭበርበር ቢሞክሩም ተጫዋቾቹ ጥያቄውን ውድቅ በማድረጋቸው ድርጊቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
በሌላ በኩል ሙትያባ ማይክ በኪታራ እና በኤክስፕረስ ጨዋታ ውጤት ማጭበርበር ውስጥ በመሳተፍና ሁለት ተጫዋቾችን በሜዳ ላይ ማጭበርበሩን እንዲፈጽሙ በመመልመል ጥፋተኛ በመባላቸው ለ10 ዓመታት ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ታግደዋል። በተመሳሳይ ጉዳይ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ተጫዋቾች ምባዚራ አሽራፍ እና የቀድሞ የሲዳማ ቡና የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል የተለያየ ቅጣት ተላልፎባቸዋል። በዚህም ምባዚራ አሽራፍ ክሱን ያስተባበለ ከመሆኑም በላይ በችሎቱ ላይ ባለመገኘቱ ለ5 ዓመታት ሲታገድ በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጫወተው ኢማኑኤል ካል ግን በምርመራው ወቅት ሙሉ ትብብር በማድረጉ፣ ጥፋቱን በማመኑ እና በክለቡ ኃላፊዎች ትዕዛዝ መንቀሳቀሱን ከግምት ውስጥ ገብቶ የ1 ዓመት እገዳው በዕግድ ተይዞለታል። በዚህም መሠረት ኢማኑኤል ካል በእገዳው ጊዜ ውስጥ ሌላ ተመሳሳይ ጥፋት እስካልፈጸመ ድረስ ወዲያውኑ ወደ እግር ኳስ እንቅስቃሴ መመለስ እንደሚችል ተገልጿል።
በመጨረሻም ኮሚቴው እንዳስታወቀው በሁሉም ግለሰቦች ላይ ከተላለፈው የእገዳ ዘመን ውስጥ ከዚህ ቀደም በእገዳ ላይ የቆዩበት ጊዜ ተቀናሽ ይደረጋል። የቅጣት ውሳኔው ለእያንዳንዳቸው ግለሰቦች በግል የተላከላቸው ሲሆን በውሳኔው ቅር ከተሰኙ በዩጋንዳ እግር ኳስ ማኅበር ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ (FUFA Appeals Committee) ይግባኝ የማለት መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ማኅበሩ ይፋ አድርጓል።

