ፕሪሚየር ሊግ፡ የሊጉ መሪ ነጥብ ሲጥል ደደቢት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል ፣ ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅም አይሏል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት 3 ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ደደቢት እና አዳማ ከተማ ድ ቀንቷቸዋል፡፡ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጥል የውድድር ዘመኑ 3ኛ ሐት-ትሪክም ተመዝቧል፡፡

በ09፡00 አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ፈጣን እንቅስቃሴ ፣ የግብ ሙከራወች እና ጥቂት ግርግሮችን  ባስተናገደው ጨዋታ የግብ ማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰዱት አርባምንጭ ከተማዎች ናቸው፡፡ በ36ኛው ደቂቃ ተሾመ ታደሰ ከእንዳለ ከበደ የተሸገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፎ አዞዎቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በአርባምንጭ ከተማ መሪነት ተጠናቋል፡፡

PicsArt_1465493883503

በሁለተኛው አጋማሽ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተሸጋሪ እና የቆሙ ኳሶች የግብ ማቆጠር አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ግብ ለማስቆጠር ረጅም ደቂቃዎች ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ በ76ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ሁለት የጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ለአመለ ሚልኪያስ ያቀበለውን ግልጽ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶ የተመለሰው ኳስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የማዕዘን ምት ሆኗል፡፡ ከማዕዘን የተሸገረውን ኳስም ደጉ ደበበ በግንባሩ በመግጨት የሊጉን መሪ አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ በካታንጋ ከጨዋታው መጀመርያ ጀምሮ በመበሻሸቅ ላይ በነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ደጋፈዎች መካከል ግርግር የተከሰተ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሎች በፍጥነት አረጋግተውት ጨዋታው ቀጥሎ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡

PicsArt_1465493819885

አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሚካኤል ጆርጅ ብቸኛዋን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ውጥረት በተሞላበት ጨዋታ በ26ኛው ደቂቃ ሱሌይማን መሃመድ በሽመልስ አበበ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን የድሬደዋ ከተማ ተጨዋቾች ግልፅ የሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል በፌዴራል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

PicsArt_1465493595758

በ11፡30 ደደቢት ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል ዳሽን ቢራ ላይ አስመዝግቧል፡፡ ዳሽን ቢራ በየተሻ ግዛው አማካኝነት የግብ ማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰደ ሲሆን አጀማመሩም ጨዋታውን በድል የሚወጣ አስመስሎት ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ወደ ጨዋታው ሪትም መግባት የቻሉት ደደቢቶች በዳዊት ፍቃዱ አማካኝት ባገኙት የአቻነት ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ደደቢቶች በቀላሉ የዳሽን ቢራን የተከላካይ ክፍል መስበር የቻሉ ሲሆን ዳዊት ፍቃዱ ከርቀት የመታው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ደደቢትን መሪ አድርጓል፡፡ ሳሚ ሳኑሚ በ78ኛው ደቂቃ 3ኛውን ሲያክል ጨዋታው ሊገባደድ የሴኮንዶች እድሜ ሲቀረው የእለቱ ኮከብ ዳዊት ፍቃዱ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በደደቢት 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ደደቢት ከ6 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል የመለሰውን ውጤት ሲያስመዘግብ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ተክተው በጊዜያዊነት ለተረከቡት አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም በመጀመርያ ጨዋታ የመጀመርያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የዳዊት ፍቃዱ ሐት-ትሪክም ከኤዶም ሆሶውሮቪ እና ሳዲቅ ሴቾ በመቀጠል በውድድር ዘመኑ የተመዘገበ 3ኛ ሐት-ትሪክ ሆኗል፡፡

PicsArt_1465489727303 PicsArt_1465493494343

የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ነገ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሲደረጉ በ09:00 ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና ፣ 11:30 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *