ዋልያዎቹ ከቻን ውጪ ሆነዋል

​በ2018ቱ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) የመጨረሻ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ በኪጋሊ ብሔራዊ ስታዲየም የሩዋንዳ አቻውን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለግብ አቻ ተለያይቶ በድምር ውጤት ከውድድሩ ውጪ ሆኗል። 

ግብፅ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ወደ ውድድሩ ለማምራት ሌላ ዕድል ያገኙት ሁለቱ ቡድኖች ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ጨዋታ 3-2 የተሸነፉት ዋልያዎቹ ከአንድ በላይ ግብ በማስቆጠር ውጤቱን ለመቀልበስ አስበው ወደ ሜዳ ቢገቡም ይህንን ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል።

አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለ4-3-3 በሚጠጋ ቅርፅ ሳምንት ሽንፈት ካጋጠመው ቡድናቸው ላይ መጠነኛ ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በግብ ጠባቂ ቦታ ጀማል ጣሰው ለዓለም ብርሃኑን ተክቶ ሲገባ በመጨረሻ ሰዓት የፓስፖርት ችግሩ ተፈትቶለት ወደ ሩዋንዳ ያቀናው የጅማ አባጅፋሩ ኄኖክ አዱኛ በቀኝ ተከላካይ ስፍራ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል። በመጀመሪያው ጨዋታ ጉዳት ያጋጠመው አስቻለው ግርማ ደግሞ በዳዋ ሁጤሳ ተተክቷል።

ዋልያዎቹ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን በ10ኛው ደቂቃም ጌታነህ ከበደ ያደረገው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወደውጪ ወጥቷል። ሩዋንዳዎች በኤሪክ ሩታንጋ እና ሚኮ ጀስቲን አማካኝነት ያደረጓቸው ሙከራዎች በጀማል ጣሠው ጥረት ሲከሽፉ በ33ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን በሩዋንዳ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች አለመግባባት ምክንያት ያገኘውን ወርቃማ ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች አስቻለው ታመነ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት በምንተስኖት አዳነ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ በቀለ ቀይረው ወደ ሜዳ ያስገቡት ዋልያዎቹ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ግን ለማድረግ ተቸግረው ታይተዋል። ጌታነህ ከበደ፣ አቡበከር ሳኒ እና ዳዋ ሁጤሳ ከርቀት ወደግብ የመቷቸው ኳሶች ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሲሆኑ ሙሉዓለም መስፍን በግንባር የሞከረው ኳስ በሩዋንዳው ግብ ጠባቂ ኤሪክ ንዳይሺሚዬ ተይዞበታል። በአንፃሩ ጀማል ጣሠው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን በቲዬሪ ማንዚ፣ ሙሃጅር ሃኪዚማና እና ሚኮ ጀስቲን ያደረጋቸውን ሙከራዎችን በማክሸፍ ስራ በዝቶበት ነበር። በተለይ በ77ኛው ደቂቃ ከሚኮ ጀስቲን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የተሞከረበትን ኳስ የመለሰበት መንገድ አድናቆት የሚገባው ነበር።

ጨዋታው ያለግብ መጠናቀቁን ተከትሎ በቅፅል ስማቸው ተርቦቹ ተብለው የሚታወቁት ሩዋንዳዎች 3-2 በሆነ የድምር ውጤት ድል ወደ ውድድሩ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። በሞሮኮ አዘጋጅነት የሚደረገው የ2018ቱ የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና ጥር 4 ሲጀመር የምስራቅ አፍሪካ ክልል በዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ሩዋንዳ የሚወከል ሲሆን ባለፉት ሁለት የቻን ውድድሮች ተሳታፊ የነበሩት እና በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ዋልያዎቹ ጨዋታዎቹን በቴሌቪዥን መስኮት ለመከታተል ተገደዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከጨዋታው በኋላ ለሩዋንዳ ሚዲያዎች አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ፎቶዎቹን ለሶከር ኢትዮጵያ በመላክ የተባበረን ሩዋንዳዊው ጋዜጠኛ ጂያን ሉክ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *