ሪፖርት | ፉክክር አልባው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የግብ ሙከራዎች ባልነበሩበት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

አርባምንጭ ከተማዎች ሀዋሳን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ፀጋዬ አበራ እና ኤሪካ ካፓይቶን አስወጥተው በምትካቸው ሙና በቀለ እና በላይ ገዛኸኝን ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ በሲዳማ ቡና ተሸንፈው የመጡት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ መልካሙ ቦጋለ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ቢኒያም ፍቅሬን አስወጥተው በምትካቸው ደጉ ደበበ፣ ያሬድ ዳዊት እና ስንታየሁ መንግስቱን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ማስጀመር ችለዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ይበልጥ አውንታዊ መሆንን የመረጡት አርባምንጭ ከተማዎች በተሻለ ኳሱን በመቆጣጠር እንዲሁም ደግሞ በሜዳው የላይኛው ክፍል ጫና በማሳደር የድቻን ተጫዋቾች ስህተት ውስጥ በመክተት ከሚገኙ ኳሶች የማጥቃት ፍላጎት እንደነበራቸው ተመልክተናል። በ2ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች በኳስ ምስረታ ሂደት አናጋው ባደግ ከሰራው ስህተት የተገኘውን ጥሩ እድል አህመድ ሁሴን በቀላሉ ለግብ ጠባቂው ባሳቀፋት አጋጣሚ የጀመረው ጥረታቸው በተመሳሳይ በ12ኛው ደቂቃም እንዲሁ አናጋው ባደግ ከሰራው የማቀበል ስህተት በተመሳሳይ ያገኙትን አጋጣሚ አህመድ ሁሴን ዳግም አምክኗል።

በአንፃሩ በኋላ መስመራቸው ላይ ኳሶችን በማንሸራሸር አርባምንጮችን ወደ ፊት በመጋበዝ ከጀርባ ትተው የሚወጡትን ክፍት ሜዳ በረጃጅም ኳሶች የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች በተለይ ከጉዳት የተመለሰውን ስንታየሁ መንግስቱን ታሳቢ ያደረጉ ተደጋጋሚ ኳሶችን ሲጥሉም አስተውለናል። በዚሁ ሂደት በተለይ በአንድ አጋጣሚ እንድሪስ ሰዒድ ለስንታየሁ መንግስቱ አሳልፎለት ሳይጠቀምበት ከቀረው ኳስ ውጭ በማጥቃቱ ረገድ ደከም ያሉ ነበሩ።

ከተጠበቀው አንፃር በተወሰነ መልኩ ክፍት ይመስል በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች እንደ ቡድን በማጥቃት ረገድ ራሳቸውን ለመግለፅ የተቸገሩ እንደነበሩ በስፋት ያስተዋልንበት አጋማሽ እምብዛም ሙከራዎች ያልነበሩበት ሆኖ አልፏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ጥቃት የፈፀሙት ድቻዎች ነበሩ። በዚህም በ48ኛው ደቂቃ አናጋው ባደግ ከመስመር ተሻምቶ በግንባር የተመለሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ በመጠበቅ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡ ይስሐቅ ይዞበታል። በዚህ ሙከራ ያላበቁት የአሠልጣኝ ፀጋዬ ተጫዋቾች ከደቂቃም በኋላ ከመስመር በተነሳ ኳስ ሌላ ሙከራ ለማድረግ ጥረው ተመልሰዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደከም ብለው የታዩት አርባምንጮች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስገባት ከወገብ በላይ ለመበርታት ሞክረዋል። በተለይ ፈጣን ተጫዋቾችን አስገብተው በመስመር በኩል ለማጥቃት ሲዳዱ አስተውለናል። በዚህም አሸናፊ ኤልያስ ከመስመር ያሻገረው ጥሩ ኳስ በላይ ገዛኸኝ ከማግኘቱ በፊት ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ በጥሩ ሁኔታ አወጣው እንጂ መሪ ሊሆኑ ነበር። በተቃራኒው ግን ከደቂቃ በኋላ ስንታየሁ በሞከረው ኳስ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር።

ጨዋታው 82ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ለግብ የቀረበ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም ወደ ድቻ የግብ ክልል የተላከውን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት አብነት ተሾመ አግኝቶ ያሻማውን ጥሩ ኳስ አሸናፊ ኤልያስ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ላይ ወጥቶችለዋል።

የዳኛው ፊሽካ ሊሰማ ከ10 ያነሱ ሰከንዶች ሲቀሩ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አሸናፊ ኤልያስ ከሳጥኑ አቅራቢያ አክርሮ የመታውን ኳስ ቢንያም ገነቱ በግሩም ሁኔታ ጨርፏት ቋሚውን ለትሞ ወጥቷል። ጨዋታውም ያለ ጎል ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ጨዋታው ሲጀምር የያዙትን አንድ ነጥብ ከጨዋታው በኋላም ይዘው የወጡት አርባምንጭ እና ድቻ በ31 እና 37 ነጥቦች በቅደም ተከተል 8ኛ እንዲሁም 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።