በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ሀዋሳ ከተማ
በምድብ ሁለት የአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከድል መልስ የመጡትን ሐይቆቹን ከሽንፈት ከተመለሱት ምዓም አናብስት ጋር ያገናኛል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከመመራት ተነስተው በያሬድ ብሩክ ሁለት ግቦች ታግዘው ውጤቱን በመቀልበስ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በዚኛው ሳምንት መርሐግብር ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ወሳኝ ግጥሚያ ያደርጋሉ። ሀዋሳ ላይ እየተደረገ ባለው የምድብ ሁለት ጨዋታ ላይ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እየተመሩ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት ሐይቆቹ ዛሬ 10:00 ሲል ምዓም አናብስቶቹን የሚያስተናግዱ ሲሆን ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ ዘጠኝ ከፍ ለማድረግ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተቃራኒው በአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የሚመሩት ምዓም አናብስት በሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት ከመምራት ተነስተው በድሬዳዋ ከተማ 2-1 የተሸነፉ ሲሆን ካስተናገዱት ሽንፈት በመላቀቅ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከሐይቆቹ ጋር ቀላል የማይባል በፉክክር የታጀበ ጨዋታን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ባሳለፈው ሳምንት ጉዳት ካስተናገደው እስራኤል እሸቱ በስተቀር ሁሉም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በተመሳሳይ በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ሁሉም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ቡድኖቹ ከተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ውጭ በሊጉ ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን እኩል ሁለት ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ፤ ሁለት ጨዋታ ደሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ መድን
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ምክትል አሰልጣኝ የነበረውን ካሊድ መሐመድን ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በምድብ አንድ ተደልድለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያዩ ሲሆን በአጠቃላይ ቡድኑ ካደረገው ሶስት ጨዋታዎች ውስጥ ምንም ጨዋታ ድል ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን ከዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማግኘት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ላይ ሀገራችንን ወክለው ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ላይ በግብፁ ፒራሚድ ቡድን 3-1 በሆነ ድምር ውጤት ከውድድሩ የተሰናበቱት ኢትዮጵያ መድኖች ፊታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ ውድድር በማዞር በዛሬው ዕለት ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሚያደርጉ ይሆናል። በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እየተመሩ የዓምና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን መሆን የቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በሁለተኛ ጨዋታቸው የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማሳካት ብርቱ ፉክክርን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ጨዋታውም ከቀኑ 7:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ኤልያስ አህመድ በቅጣት ምክንያት የማይኖር ሲሆን ጉዳት ላይ የነበሩት ኢዮብ ዓለማየሁ እና ቃለአብ ውብሸት የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በኢትዮጵያ መድን በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ኢትዮጵያ መድን አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዲያ ሆሳዕና በአንድ ጨዋታ አሸንፎ የተቀረው በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። አስራ ሁለት ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነት ኢትዮጵያ መድን ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሸገር ከተማ
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ካደረጓቸው 2 ጨዋታዎች ሁለቱንም ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በሁለተኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር የነበራቸውን ጨዋታ መርሐግብር ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን በሊጉ በሰበሰቧቸው ስድስት ነጥቦች ሰባተኛን ደረጃ ይዘው የሚገኙ ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ድል በማድረግ የማሸነፍ ሪከርዳቸውን ለማቀጠል ከአዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ሸገር ከተማዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ሁለት ጨዋታዎችን በማድረግ አንድ ተስተካካይ መርሐግብር ያላቸው ሲሆን እስካሁን ካደረጓቸው ጨዋታወች ውስጥ ማሸነፍ ያልቻሉ ሲሆን ከዛሬውን ጨዋታ የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማግኘት ከፈረሰኞቹ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ተገናኝተው የማያውቁ ሲሆን ይህም የመጀመሪያቸው ይሆናል።


