ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል

ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ4ኛው ሳምንት የምድብ ሁለት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ መድን

በእንቅስቃሴም ይሁን የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በአጋማሹ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት ነብሮቹ ተመስገን ብርሀኑ ከግቡ አፋፍ ባደረገው እንዲሁም ፀጋአብ ከቆመ ኳስ መቶት በፋሲል ገብረሚካኤል በተመለሱ ሁለት ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። አለን ካይዋ ከወገኔ ገዛኸኝ የተቀበላትን ኳስ መቶት ተከላካዮች ተደርበው ባወጡት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበሩት መድኖችም በ28 ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ያሬድ ካሳዬ አሻምቶት ረመዳን የሱፍ በግንባር ገጭቶት ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ በድንቅ ብቃት ከመለሰው በኋላ አለን ካይዋ በግንባር ያስቆጠረው ግብም መድንን መሪ ማድረግ ችሏል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ብሩክ በየነ በመልሶ ማጥቃት ከጸጋአብ ዮሐንስ ያገኛትን ኳስ በጥሩ መንገድ ሰንጥቋት ተመስገን ብርሃኑ ከመረብ ጋር ያዋሃዳት ኳስም ነብሮቹን አቻ ማድረግ ችላለች።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቃዛ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ግን ጥቂት ነበሩ። በሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል መሱ ከቤላ እንዲሁም አሸናፊ ኤልያስ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች በኢትዮጵያ መድኖች በኩል ደግሞ ዋንጫ ቱት ከመዓዝን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው አስቆጪ ሙከራ ይጠቀሳሉ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት 89ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ ወደ ሳጥን አሻምቶት ዳግም ንጉሤ ወደ ራሱ መረብ ባስቆጠረው ግብ መድኖች መሪ መሆን ችለዋል። በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ ፉክክር በተደረበት ጨዋታም ኢትዮጵያ መድን የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሸገር ከተማ

ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ  ቢሆንም ወደ ግብ ደርሶ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ ግን ሸገር ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። በፈረሰኞቹ በኩል ፍፁም ጥላሁን ከመስመር አሻግሮት አቤል ያለው  ከመምታቱ በፊት ዘነበ ከድር ተደርቦ ያወጣው እንዲሁም ፍፁም ጥላሁን እና አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውጭ አክርረው በመምታት ያደረጓቸው ሙከራዎች ሲጠቀሱ በሸገር ከተማዎች በኩልም በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ዘነበ ከድር ከመስመር አሻግሯቸው ያሬድ መኮንን እና  አንተነህ ተፈራ በግንባር ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ሁለተኛው አጋማሽ በፉክክር ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ቢሆንም በሙከራዎች የረገድ ግን ውስን መቀዛቀዞች የታዩበት ነበር። አጋማሹ በተጀመረ በመጀመሪያው ደቂቃም ሄኖክ አዱኛ ከቆመ ኳስ አሻምቷት ያሬድ መኮንን ከመረቡ ጋር ያዋሃዳት ኳስ ሸገር ከተማዎችን መሪ ማድረግ ችላለች። ፈረሰኞቹ ከግቧ መቆጠር በኋላ በተሻለ መንገድ ለማጥቃት ጥረት ማድረግ ቢችሉም ቢኒያም ፍቅሩ ከመስመር የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ካደረጋት እጅግ አስቆጪ ሙከራ ውጭ የጠራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በጥሩ መንገድ በተከላከሉት ሸገር ከተማዎችም ሄኖክ ከመስመር አሻግሯት ጀቤሳ አክርሮ በመምታት ያደረጋት ሙከራ ትጠቀሳለች። ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታም ሸገር ከተማዎች ድል በማድረግ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።