ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከድል ጋር ታርቋል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከድል ጋር ታርቋል

አዳማ ከተማዎች ከ293 ደቂቃዎች በኋላ ባስቆጠሩት ጎል አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 አሸንፈዋል።

በዋና ዳኛ ባሕሩ ተካ መሪነት 9 ሰዓት ሲል በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ሆኖም 24ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ከናፈቃቸው ጎል ጋር ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ የታረቁበትን አጋጣሚ አግኝተዋል። ነቢል ኑሪ ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን ሲገባ አሸናፊ ፊዳ ከኋላ ጎትቶ በመጣሉ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቢኒያም ዐይተን በአግባቡ ተጠቅሞ አስቆጥሮታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እጅግ የተቸገሩት አርባምንጮች ይባስ ብሎም 40ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ፊዳን በሁለት ቢጫ ካርዶች አጥተዋል። ተከላካዩ በአዳማው አማካይ ሀይደር ሸረፋ ላይ በሠራው ጥፋት ነው ከሜዳ የተወገደው።

አዞዎቹ ወደ ሳጥን ገብተው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢቸገሩም 44ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። የመስመር ተጫዋቹ ኤፍሬም ታምራት ከረጅም ርቀት በድንቅ ሁኔታ የመታው ኳስ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ቀጥሎ በአርባምንጭ ከተማ በኩል በፍቅር ግዛው 54ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል የወጣበት በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን በተሰነጠቀለት ኳስ ወደ ሳጥን ጠርዝ ሲደርስ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ የመለሰበት ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 6 ደቂቃዎች የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ጄሮም ፊሊፕ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያመቻቸውን ኳስ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው ይህም የተሻለው የመጨረሻው ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።