በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የ2ኛ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአቤል ሀብታሙ ብቸኛ ግብ ምድረገነት ሽረን ሲረታ ድሬዳዋ ከተማም ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ምድረ ገነት ሽረ
በመጨረሻዎቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱ ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የታየበት ቢሆንም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ግን ምድረ ገነት ሽረዎች የተሻሉ ነበሩ።
ስንታየሁ ወለጬ በረዥሙ አሻግሯት ዳንኤል ዳርጌ
በጥሩ መንገድ አፈትልኮ ከፍ አድርጎ የሞከራት ኳስ እንዲሁም ራሱ ዳንኤል ዳርጌ ሳይጠበቅ ከርቀት ያደረጋት ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። ከማዕዝን ተሻግራ ሽመክት ጉግሳ ከጨረፋት በኋላ ዳንኤል ዳርጌ ያደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ እንዲሁም ተካልኝ ደጀኔ አመቻችቷት አቤል ማሙሽ በጥሩ መንገድ ከመታት በኋላ ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስም ዕድሎች በመፍጠር በኩል ብልጫ በነበራቸው ሽረዎች የተደረጉ ሌሎች ሙከራዎች ናቸው።
በፍቃዱ አስረሳኸኝ በምድረ ገነት ሽረ ተከላካይ ስህተት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ኳስም በአጋማሹ ጥቂት የግብ ዕድሎችን ለፈጠሩት ኤሌክትሪኮች መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

በብዙ መለኪያዎች ቀዝቃዛ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩበት ነበር። አቤል ሀብታሙ ከተከላካይ ጀርባ በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት አጋጣሚም በአጋማሹ ከተደረጉ ሙከራዎች ውስጥ የተሻለ ለግብ የቀረበች ናት። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩት ግን ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የቀረቡት ኤሌክትሪኮች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አቤል ሀብታሙ ተቀይሮ ከገባው ፓትሪክ ሲቦማኔ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባለድል ያደረገች ግብ ነበረች።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ
ቡናማዎቹ እና ብርቱካናማዎቹን ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር በመጀመርያው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር እና በርካታ የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር።
ዕድሎች በመፍጠርም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ቡናማዎቹም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በዘላለም አባተ አማካኝነት መሪ ለመሆን የተቃረቡባቸው ሦስት አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል። ተጫዋቹ ከአቡበከር አዳሙ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እና ከመስመር ተሻግራ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያገኛት ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ ያደረጋት ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። አስራት ቱንጆ በራሱ ጥረት ያገኛትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ከመለሳት በኋላ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ አቤል ነጋሽ ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራም ለድሬዳዋ ከተማ አስቆጪ ሙከራ ነች።
በ31ኛው ደቂቃም አቡበከር አዳሙ ከሳጥኑ የግራ ክፍል አክርሮ በመምታት ያስቆጠራት ማራኪ ግብ
ብልጫ ለነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ቡናማዎች ዘላለም አባተ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣች ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲቃረቡ ግሩም መኩርያ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ገፍቶ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት እንዲሁም መሐመድኑር ናስር ወደ ሳጥን አሻግሯት ግብ ጠባቂው ከመለሳት በኋላ በግቡ ቅርብ ርቀት የነበረው አስራት ቱንጆ ያልተጠቀመባት ዕድልም ብርቱካናማዎቹን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሁለት አጋጣሚዎች ናቸው።

ድሬዳዋ ከተማዎች ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ማራኪ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች አቡበከር አዳሙ መቷት አብዩ ካሳዬ ወደ ውጭ ባወጣት ኳስ የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በተቀሩት ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎች የፈጠሩት ግን ድሬዳዋ ከተማዎች ነበሩ። በ77ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ አስራት ቱንጆ በጥሩ መንገድ አሾልኳት ጀሚል ያዕቆብ ወደ ግብነት በቀየራት ኳስ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ቡናማዎቹ ሻባን መሐመድ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መቷት አብዩ ካሳዬ በጥሩ መንገድ ባዳናት ሙከራ መሪ ለመሆን ቢቃረቡም ከደቂቃዎች በኋላ ድሬዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። መሐመድኑር ናስር ተቀይሮ የገባው አብዲሳ ጀማል ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች።
ጨዋታው ከመጠናቀቁ ከደቂቃዎች በፊት አብዲሳ ጀማል በመልሶ ማጥቃት አግኝቷት ከግብ ጠባቂ አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ካመከናት ወርቃማ ዕድል በኋላም 14 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች እና ማራኪ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

