መረጃዎች| የ12ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች| የ12ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

12ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐ-ግብሮች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እነሆ!

ድሬዳዋ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ

በደረጃ ሰንጠረዡ እኩል 16 ነጥብ በመያዝ በ8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማ እና ነጌሌ አርሲ የ12ኛ ሳምንት መርሐ-ግብራቸውን ዛሬ ያከናውናሉ። በ16 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በማሸነፍ ለአምስት የጨዋታ ሳምንታት ዘልቆ የነበረውን የድል አልባ ጉዞ መግታታቸው ይታወሳል። ቡድኑ ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ያገኘውን ወሳኝ ድል የሚፈጥርለትን መነቃቃት በመጠቀም በደረጃ ሰንጠረዡ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ የሚገኘውን ተጋጣሚውን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባል።

ከተጋጣሚያቸው በእኩሌታ 16 ነጥብ በመሰብሰብ በግብ ልዩነት በልጠው በ8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዲስ አዳጊዎቹ ነጌሌ አርሲዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ባሳለፍነው ሳምንት መርሐ-ግብር ወልዋሎን 1- 0 በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ማሳካት የቻሉት ሰጎኖቹ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ ፍልሚያው ወሳኝ ነው። በተጨማሪም ቡድኖቹ ካላቸው ወቅታዊ መነቃቃት አንጻር ፍልሚያው በፉክክር የታጀበ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ሳምንታት በጉዳት ግልጋሎታቸውን ካላገኘባቸው አቤል አሰበ እና አስቻለው ታመነ በተጨማሪ ጀሚል ያቆብንም በጉዳት በዛሬው ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን አብዱልሰላም የሱፍ ግን ከአንድ ጨዋታ ቅጣት በኋላ ለፍልሚያው ዝግጁ እንደሆነ ታውቋል። ነገሌ አርሲዎች አሁንም የዓብዱልባሲጥ ከማል ግልጋሎት አየገኙም ከዚህ በተጨማሪ የኢብሳ በፍቃዱ መሰለፍም አጠራጣሪ ሲሆን ተከላካዩ ዴሲሬ ፓስካል ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ታሪክ ሲገናኙ የዛሬው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ከአሸናፊነት የተመለሱት ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያስመዘገቡትን ተከታታይ ድል ለማስቀጠል ዛሬ ይፋለማሉ። በ20 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች የውጤት ማጣት በኋላ በሊጉ ጥሩ የሚባል መነቃቃት እያሳዩ ይገኛሉ። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ድል ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን በተለይም በ11ኛው ሳምንት መርሐ-ግብር ከሸገር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከመመራት ተነስቶ 2-1 ማሸነፉ ለቡድኑ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረለት ሲሆን ዛሬም ይህንን የአሸናፊነት ጉዞ በመቀጠል በሰንጠረዡ አናት ያለውን ፉክክር ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በ13 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ካጋጠማቸው የሦስት ጨዋታዎች ውጤት ማጣት በኋላ ወደ ድል በመመለስ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተከታታይ ድሎችን ማሳካት የቻሉ ሲሆን በ11ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን 2-1 በማሸነፍ ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል። ሆሳዕናዎች አሁን ላይ ያላቸውን የተሻሻለ አቋም በመጠቀም ከጠንካራው ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ለመውሰድና ወደ ሰንጠረዡ መሃል ለመጠጋት ጨዋታው ወሳኝ ይሆንላቸዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በሀድያ ሆሳዕና ብሩክ በየነ እና ጄይላን ከማል በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ክለቦቹ የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሀዋሳ 4 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና 1 አሸንፏል። በቀሪ 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 18፣ ሀዲያ ሆሳዕና 14 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ሽረ ምድረ ገነት ከ አዳማ ከተማ

ባሳለፍነው ሳምንት ከሽንፈት የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች በዛሬው ጨዋታ ወደ ድል ለመመለስ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ቦታቸውን ለማሻሻል ይፋለማሉ። በ14 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሽረ ምድረ ገነቶች ለተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሳይሸነፉ ከዘለቁ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1- 0 በሆነ ጠባብ ውጤት መሽነፋቸው ይታወሳል። ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰው ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ብሎ መቀመጥን በሚያልሙበት ጨዋታም ከአዳማ ከተማ የሚጠብቃቸው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።

በ17 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። ቡድኑ በ11ኛው ሳምንት መርሐ-ግብርም በመቻል 3-1 በሆነ ውጤት ሽንፈት የደረሰበት ሲሆን ይህም በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ መሪዎች ተርታ ለመጠጋት የሚያደርገውን ጉዞ እክል ፈጥሮበታል። አዳማ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ ካጋጠማቸው የሁለት ጨዋታዎች የውጤት ማጣት ጉዞ ወጥተው ሦስት ነጥብ በማሳካት ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በሽረ ምድረ ገነት በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተው ፀጋአብ ዮሐንስ ከጉዳት ሲመለስ የናትናኤል ተኽለ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ነው። በአዳማ ከተማ ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ምክንያት የማይኖረው ሚራጅ ሰፋ ጨምሮ፣ ዳዋ ሆቴሳ፣ ጋዲሳ ዋዶ፣ አላዛር ሽመልስ እና ግብጠባቂው ናትናኤል ተፈራ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው አሜ መሐመድ ቡድኑን ተቀላቅሎ ልምምድ መስራት ጀምሯል።

በግቦች የተንበሸበሸ የግንኙነነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማዎች 2 ጊዜ ድል ሲያደርጉ ምድረ ገነት ሽረዎች በበኩላቸው 1 ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በግንኙነቱ አዳማ ከተማ 10 ምድረ ገነት ሽረ ደግሞ 6 ግቦች አስቆጥረዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ሸገር ከተማ

የሊጉን መሪነት ዳግም ለመረከብ የሚፋለሙት ሲዳማ ቡናዎች እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ የሚገቡት ሸገር ከተማዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የ12ኛው ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ነው። በ22 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሊጉ መሪ የነበሩ ቢሆንም ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በትናንትናው ዕለት ካሳካው ድል በኋላ የሊጉን መሪነት አስረክበዋል። በ11ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት የተለያየው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ሸገር ከተማን በማሸነፍ በድጋሚ የሰንጠረዡ አናት መቆናጠጥ ዋነኛ ዓላማው እንደሚሆን እሙን ነው።

በ12 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሸገር ከተማዎች በሊጉ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት በአንዱ ላይ ብቻ ነው። ይህም በቡድኑ ያለው የውጤት መቀዛቀዝ
የሚያመለክት ሲሆን በ11ኛው ሳምንት መርሐ-ግብር በሀዋሳ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ማገገምም የዛሬ ዋና ዓላማቸው እንደሚሆን ይጠበቃል። ቡድኑ መሪነቱን ለመረከብ ከሚያልመው ሲዳማ ቡና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ከስጋት ቀጠናው ርቆ በሰንጠረዡ ከፍ ለማለት ሦስት ነጥብ ማሳካት እጅግ ወሳኝ ይሆንለታል።

በሸገር ከተማ በኩል ናትናኤል ዘለቀ አምስት ቢጫ ካርዶችን መመልከቱን ተከትሎ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በሲዳማ ቡና በኩልም አጥቂው ሀብታሙ ታደሰ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ መድረክ የዛሬው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙበት ነው።