👉 “ጨዋታው እጅግ ፈጣን እና ከፍተኛ መነሳሳት የታየበት ነበር”
👉 “ዳኞች ጨዋታውን የዳኙበት መንገድ ፍትሃዊነት ይጎድለው ነበር”
በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተደረገው የኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ካሊስቶ ፓሱዋ የሰጡትን ድህረ-ጨዋታ አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
“ጨዋታው እጅግ ፈጣን እና ከፍተኛ መነሳሳት የታየበት ነበር። ሆኖም እኛ ግጥሚያውን የጀመርነው በዝግታ በመሆኑ ገና ጨዋታው በጀመረ በ35 ሰከንዶች ውስጥ በታየ የትኩረት ማጣት ሳቢያ ከቆመ ኳስ ግብ ተቆጥሮብናል። ከመጀመሪያው ደቂቃ ስህተት በኋላ ግን በሚገባ ተረጋግተን ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለናል።”
“በመጀመሪያው አጋማሽ የጎል ዕድሎችን ወደ ግብ መቀየር አለመቻላችን አሳዛኝ ነበር። በተለይም በመሃል ሜዳው ላይ ኳሶችን መልሶ በማግኘት ረገድ ክፍተቶች ነበሩብን። እግር ኳስ በዕድሎች ላይ የተመሰረተ ነው እናም ከተጋጣሚያችን የተሻሉና ግልጽ የሆኑ የጎል ዕድሎችን አግኝተን ሳንጠቀምበት ቀርተናል። በዚህ የላቀ የእግር ኳስ ደረጃ አንድ ዕድል አግኝተህ ካልተጠቀምክበት በተጋጣሚ መቀጣትህ የማይቀር ነው እኛም የሆነው ይሄው ነው።”

“የልጆቼን የውጊያ መንፈስ እና ፍላጎት በሚገባ አይቻለሁ። ጎል ከተቆጠረብን በኋላ ሳናፈገፍግ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ተጋጣሚ ክልል ለመድረስ ያደረግነው ጥረት የሚበረታታ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው የገቡ ወጣት ተጫዋቾች ማጥቃቱ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ እና ለእያንዳንዱ ኳስ ያደረጉት ተጋድሎ ለቡድኑ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው።”
“እኔ አሰልጣኝ እንጂ ዳኛ አይደለሁም ሆኖም ጨዋታውን የዳኙበት መንገድ ፍትሃዊነት ይጎድለው ነበር። ሁልጊዜም እግር ኳስ ፍትሃዊ እንዲሆን እንፈልጋለን ዳኛው ራሱ በሚቀጥሉት ጨዋታዎች ላይ ከዚህ የተሻለ መሆን እንዳለበት ራሱ ያውቀዋል ብዬ አስባለሁ።”
“ለቀጣዩ ጨዋታችን ከፍተኛ ትኩረትን ሰንቀን መግባት አለብን። የቀሩንን ጥቂት ቀናት ተጠቅመን በመሃል ክፍላችን ላይ የታዩትን ክፍተቶች በማስተካከል በቀጣዩ ጨዋታ የተሻለ ማንነት ይዘን እንቀርባለን።”

