ሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በሀገራችን ስለ ስታዲየሞች ያለውን አረዳድ የቀየረ ህያው ማሳያ

ወደ ኢትዮጵያ ትልቁ የሊግ ዕርከን ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያሉት ሀላባ ከተማዎች ወደ ሊጉ ሲመጡ ቡድናቸውን ብቻ ሳይሆን ይልቁንስ ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የሚችል አስገራሚ ስታዲየምንም ጭምር አዘጋጅተው ብቅ ብለዋል።
ስታዲየም ሲባል እጅግ ግዙፉ የአርማታ ቁልል ለሚመስለው ሀገሬው ስታዲየም ማለት መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ጥንቅቅ ያለ ግንባታ እንጂ ሲል የሀገሬውን ገዢ ሀሳብ የሞገተ ድንቅ የህብረተሰብ የጋራ አሻራን አስመልክተውናል።
ይህ “የሀላባዎቹ መንገድ” ስታዲየም እንገነባለን ብለው 50 እና 60 ሺህ ህዝብን የሚያስተናገድ ግዙፍ የኦሎምፒክ ስታንዳርድ ስታዲየምን አስበው ሩቅ አልመው ቅርብ ላደሩት ብዙሃን ታዓምር ብቻ ሳይሆን መንገዳቸውን ቆም ብለው እንዲፈትሹ ያስገደደ የታሪክ አጋጣሚ ሆኗል።
ይህ ስታዲየም ከስፓርት መሰረተ ልማትነት ባሻገር የማህበረሰብ የጋራ ቃልኪዳን ውጤት ነው ፤ የልማት ውጥኖች በመንግስት የተናጥል ጥረት ብቻ ሳይሆን በሁሉን ዓቀፍ የማህብረሰብ ንቅናቄ ጋር ሲቀናጁ በአጠረ ጊዜ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ህያው ማሳያ ነው።
10,000 ተመልካቾችን የሚያስተናግደው ይህ ስታዲየም ተመልካቾችን በማስተናገድ አቅም ከአብዛኞቹ የአርማታ ቁልሎች በቁጥር በብዙ እጥፍ ቢያንስም ጥንቅቅ ብሎ የተሰራ ሰው ሰራሽ ሜዳ ፣ ለመሮጫ ትራክ ስራ ዝግጁ የተደረገ አስፋልት ፣ በከፊል መጠለያ የተሰራላቸው የመቀመጫዎችን የያዘው ይህ ስታዲየም ከጥቂት ዓመታት በፊት ውሃ የሚይዝ አንድ መደበኛ መጫወቻ ነበር ነገርግን በሀላባ ህዝብ የተባበረ ክንድ ወደ ግሩም ስታዲየምነት ተሸጋግሯል።
በጥራት የተሰሩ ሜዳዎች እጥረት ክፉኛ ሲሰቃይ ለኖረው ሊጋችን የሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም መፍትሔ ሆኖ ብቅ ብሏል ፤ ክለቦች ሆይ ስታዲየም የስፓርት መሰረተ ልማት ለመገንባት ስታስቡ “የሀላባዎቹን መንገድ” ተጠቀሙ።
ትላልቅ ስታዲየሞች ከሚጠይቁት ከፍተኛ መዋዕለነዋይ መነሻነት በአሁናዊ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በትውልዶች ቅብብል እንጂ በአጠረ ጊዜ ማጠናቀቅ እንደ ሰማይ ርቆናልና ፤ በተለያዩ ምዕራፍ የሚገነቡ መጠነኛ ነገርግን በሂደት እያደጉ እና እየተሻሻሉ የሚመጡ ስታዲየሞችን ግንባታን እየተለማመድን መምጣት ይኖርብናል።
“የሀላባ መንገድ” ብዙዎች ሊከተሉት የሚገባ የሀገራችንን የስፓርት መሰረተ ልማት ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ የሚያስችል ውጤታማው መንገድ ይመስላል ፤ በመሆኑም ስታዲየም ለማነፅ ያሰቡ ሁሉ ከሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ብዙ ሊማሩ ይገባል።

