የኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ መካከል የእርቀ ሠላም ጉባዔ ተካሄደ

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባበት እንዲፈታ እና ወንድማማችነት እንዲኖር ኃላፊነት በመውሰድ ዛሬ ከ07:00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ያዘጋጀው የዕርቀ ሠላም ጉባዔ በስኬት ተጠናቋል።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍስሃ (ኢ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ፕሬዝደንት ፍቃደ ማሞ (መ/አለቃ)፣ የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ የበላይ ጠባቂ ክንደያ ገብረሕይወት (ፕሮፌሰር) እና የደጋፊ ማኅበር ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የዕርቀ ሠላም የውይይት መድረኩ የተካሄደው።

ሰፊ ውይይት በሁለቱም ክለቦች መካከል ከተካሄደ በኃላ የፊታችን ማክሰኞ በ10:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄደው የቡና እና መቐለ ጨዋታ በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠናቀቅ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባዔው ተጠናቋል።

1ኛ. በስፖርታዊ ውድደር ጊዜ የሚንፀባረቁ ስፖርታዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች እና ባህርያትን ሁለቱም ክለቦች ማውገዝ እና ማረም ሲገባቸው አለማድረጋቸው ክፍተቶች እንዲበዙና አለመግባባቱ እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውን አምነው ተቀብለው ለማስተካከል መግባባት ላይ ደርሰዋል።

2ኛ. ስፖርት የሠላም ፣ የፍቅር ፣ የአንድነት መገለጫ መሆን ሲገባው ከዚህ በተቃራኒ የተጓዘ በመሆኑ የክለባት ደጋፊዎቻችን ፣ የስፖርት ማኅበረሰብ እንዲሁም ህዝብን የሚያሳዝን ስለሆነ ሊታረም የሚገባው መሆኑን ከስምምነት ደርሰናል።

3ኛ. ስፖርቱን ወዳልተገባ መንገድ እንዲሄድ የተለያዩ አካላት እየተጠቀሙበት ስለሚገኝ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስፈላጊውን ስራ እንዲሰራ ሁለቱም ክለባት ከስምምነት ደርሰዋል።

4ኛ. የፊታችን ማክሰኞ ሰኔ 11 የሚካሄደው ጨዋታ ሠላማዊ ሆኖ እንዲፈፀም የሁለቱም ክለባት ደጋፊዎች ክለባቸውን በስፖርታዊ ጨዋነት ሠላማዊና ፣ በህጋዊ መልኩ እንዲደግፉ ጥሪ ተደርጓል።

5ኛ የ. ደጋፊዎች ከሚነሱበት ስፍራ ጀምሮ ሠላማዊ ጉዞ እንዲኖራቸው የሚመለከታቸው አካላትና ህዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ። ደጋፊዎችም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ፍፁም ሠላማዊ ውድድር እንዲሆን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

6ኛ. ለዚህም እንዲረዳ ከሁለቱም ክለባት 6 አባላት ያሉት እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንዲሰሩ ኃላፊነት ተሰጥቷል። በቀጣይነትም የሁለቱም ክለባት አመራሮች ዘላቂ የሆነ ወንድማማችነት እንዲኖር በጋራ ለመስራት ከውሳኔ ደርሰዋል።

በመጨረሻም የሁለቱም ክለባት አመራሮች እስካሁን ለተፈጠረው አለመግባባት ለደጋፊው እና ለህዝቡ ይቅርታ ጠይቀዋል። ነገ 07:00 ላይም በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ሁለቱም ክለቦች ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡