” የተሰጠኝ ነፃነት ውጤታማ አድርጎናል” የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ደረጄ በላይ

ሰበታ ከተማን ከ11 ዓመት በፊት፤ በቅርቡ ደግሞ ከጅማ አባ ቡና ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ችለዋል፡፡ በክረምቱ መድንን ለቅቀው ወልቂጤ ከተማን በመያዝ ከምድብ ለ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሊጉ ማሳደግ ችለዋል። ከሶስት ክለቦች ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ የታሪክ ተጋሪ የሆኑት አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ቡድናቸው አርሲ ነገሌ ላይ 1-1 ተለያይቶ አንድ ጨዋታ እየቀረው ወደ ሊጉ ማደጉን ካረጋገጠ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

” የተሰጠኝ ነፃነት ውጤታማ አድርጎኛል”

በቅድሚያ የውጤታማነታችን ሚስጥሩ ማንም ክለብ ሳይቀድመን እኛ በፍጥነት የምንፈልገውን ተጫዋች አስፈረምን። ትልቁ ነገር ስብስብ ነው። እነኛ የሰበሰብኳቸው ናቸው ይሄን ያህል ነጥብ ያመጡት። ሌላው አዲስ አበባ ስለነበርኩ የፈለኩትን ተጫዋች ለማስፈረም ነፃነት ሰጥተውኝ ነበር።

ጥሩ ቡድኖች በምድቡ በመኖራቸው እጅግ ከባድ ነበር። ስለዚህ የኛ ዕቅድ የነበረው ከመጨረሻ መርሐ ግብሮች ከሜዳ ውጪ አራት ነጥብ፤ በሜዳችን ስድስት ነጥብን ለማግኘት ነበር። የሚገርመው ከአንደኛው ዙር ጀምሮ ደግሞ ይህ ነበር ስናሳካ የነበረው። ዛሬ (እሁድ) ከፍተኛ ጫና ውስጣችን ስለነበረ በእልህ ተጫውተን አሸንፈናል። ከሁሉም በላይ ግን ፈጣሪን እና ባለቤቴን አመሰግናለሁ። ባለቤቴ አዲስ አበባ ናት፤ ልጆች ቢታመሙ እንኳን እንዳልጨነቅ ምንም አይነት ጫናዎች እንዳይኖሩብኝ ታስባለች። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ከጫናዎች ነፃ እንድሆን ስላደረጉኝ በተጨማሪም የስራ አስፈፃሚ አባላት ነፃነት ስለሰጡኝ ተሳክቶልኛል። ደጋፊውም በደንብ አግዞናል፡፡

“ማሸነፍ እና ዋንጫ ማንሳት አይጠገብም”

ማሸነፍ እወዳለሁ፤ አሰልጣኝ ደግሞ ሲሳካለት ደስ ይለዋል። እኔ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ ወልቂጤን ይዤ አሳድጊያለሁ። መጀመሪያ ሰበታን፣ ቀጥሎ ጅማ አባ ቡና እና አሁን ደግሞ ወልቂጤን… ይህን ስታደርግ ስሜቱ የተለየ ነው። ለምሳሌ እኔ አርሲ ነገሌን ብይዝ እንኳን ማሸነፍን ነው የማስበው። በኔ እይታ ደግሞ ማሸነፍ እና ዋንጫ ማንሳት አይጠገብም። እንጀራዬ ስለሆነ ጠንክሬ እሰራለሁ። ለዚህም ነው የሚሳካልኝ።

” ከኔ የሚጠበቀውን መቶ በመቶ አሳክቻለሁ”

መጀመሪያ ሲቀጥሩኝ የተነጋገርነው መቶ በመቶ ቡድኑን ለማሳደግ ቃል ገብቼ ነበር። ከኔ የሚጠበቀውን መቶ በመቶ አሳክቻለሁ። ከነሱ የሚጠበቀውንና የሚያደርጉልኝን ደግሞ በተስፋ እጠብቃለሁ (ሳቅ)። እኔ የምሰራሁ ሁልጊዜ ለመሸለም ነው። ያን ስለምወድ ደግሞ ሊሸልሙኝ ተዘጋጅተዋል፡፡

” ሊጉ ምን ይፈልጋል በሚለው ዙርያ የክለቡ አመራሮች በንቃት ሊዘጋጁ ይገባል”

ታስታውስ እንደሆነ አባቡናን ይዤ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስንገባ ሌሎቹ ተዘጋጅተው ከጨረሱ በኃላ ነው በቶሎ ወደ ዝግጅት የገባነው። ዘንድሮ ግን ጥሩ ነው፤ ወልቂጤ በሊጉ ተፎካካሪ ለመሆን ካለፈው የውድድር ዓመታት አንፃር የተሻለ የመዘጋጃ ጊዜ አለው። ስለዚህ በጊዜ የሚያስፈልገውን ሊጉ ምን ይፈልጋል የሚለውን የክለቡ አመራሮች በንቃት ሊዘጋጁበት ይገባል፡፡ እኔ ግን ልቀጥል አልቀጥል አላውቅም፤ ኮንትራቴ አልቋል። አሁን ያለው ነገር ግን ጥሩ ሂደት ላይ ነው።

ካስፈለገዎ: ወልቂጤ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡