ድሬዳዋ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ውል አራዘመ

ብርቱካናማዎቹ የአንተነህ ተስፋዬ እና የሳምሶን አሰፋ ውል አራዝመዋል።

የቀጣይ ዓመት ስራቸውን የአሰልጣኙ ስምዖን ዓባይን ቆይታ በማስቀጠል የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች የተከላካይ ክፍል ወሳኝ ተጫዋቻቸው የሆኑት አንተነህ ተስፋዬ እና ሳምሶን አሰፋን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት አድሰዋል።

በ2009 ክረምት ሲዳማ ቡናን ለቆ የምስራቁን ክለብ የተቀላቀለው አንተነህ ወጥነት ጥሩ ብቃት ሲያሳይ የቆየ ሲሆን ውሉን ማራዘሙም ቡድኑ የተረጋጋ የተከላካይ መስመር እንዲኖረው ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ግብ ጠባቂው እና የቡድኑ አምበል የሆነው ሳምሶን አሰፋም ውሉን ማደሱ ድሬዳዋን በሊጉ ከሚገኙ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎችን በመደበኛ ተሰላፊነት ከሚጠቀሙ ክለቦች አንዱ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችለዋል።

ባለፈው ዓመት በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር በመለያየታቸው የቡድን ጥልቀት ችግር አጋጥሟቸው ተጨዋቾችን በውሰት ለማምጣት የተገደዱት ብርቱካናማዎቹ በቀጣዮቹ ቀናት አዳዲስ ተጫዋቾች ያዘዋውራሉ ተብሎ ሲጠበቅ በሁለተኛው ዙር ወደ ጥሩ ብቃት መጥቶ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆን የቻለው አማካዩ ረመዳን ናስርን ውል ለማራዘምም ተቃርበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡