” …እኔ ተሸንፈናል ብዬ አላስብም” የጅቡቲ አሰልጣኝ ጁሊያ ሜት

ከትናንት በስቲያ ለቻን 2020 የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጎረቤት ሃገር ጅቡቲን በደርሶ መልስ የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጠቃላይ 5-3 በሆነ ድምር ውጤት ለቀጣዩ ማጣሪያ አልፏል፡፡ ጅቡቲ ላይ ጎል ማግባት ተቸግሮ የነበረው ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻ በአስቻለው ታመነ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል 1-0 አሸንፎ በመልሱ ደግሞ ድሬ ዳዋ ላይ ደግሞ በጅቡቲ ተፈትኖ 4-3 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ የማጣሪያ ዙር አልፏል፡፡ ከጨዋታው በኋላ የጅቡቲው አሰልጣኝ ጁሊያ ሜት ከሶከር ኢትዮጵያ ፈረንሳይኛ አዘጋጅ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

የድሬዳዋውን ጨዋታ እና ውጤቱን እንዴት አገኙት?

ውጤቱን በተመለከተ ቢያንስ አቻ ይገባን ነበር። 3ለ3 ሆነን 88 ወይም 89ኛው ደቂቃ ላይ በገባብን ጎል ተሸንፈናል፤ በተለይ አቻ ከሆንን በኋላ 4-3 የምንሆንበትን ዕድል ማባከናችን የሚያስቆጭ ነው፡፡ በውጤቱ በጣም አዝኛለው። እንዳየኸው የኛ ልጆች ከጨዋታው በኋላ ሜዳ ላይ ሲያለቅሱ ነበር፡፡ በእግር ኳስ አይሆንም የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሜዳ 3 ማግባት ቀላል አይደለም፤ ይህንን በቅርብ ጊዜ ማድረግ የቻለው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ ነበር፣ ይህን አሳክተናል፡፡ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ አምበላችንን ጨምሮ የተጎዱብን ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ በተለይ መከላከሉ ላይ በጣም ጥሩ ነበርን፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ምንም ነገር መፍጠር እንዳይችል አስበን ገብተን ተሳክቶልናል፡፡ የሁለቱንም ቡድኖች ከተመለከትክ የተጋጠምነው ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ልጆች ጋር ነው፡፡ የተጫዋቾቹን ተክለ-ቁመና ካየህ ደግሞ የኛ ልጆች በጣም ደቃቃ ናቸው፡፡ ጨዋታው ላይ ግን የበለጠ የጨዋታ ብቃትና የማሸነፍ ፍላጎት የነበረው ግን የኛ ልጆች ጋር ነው፡፡ በተጫዋቾቼ በጣም ኮርቻለው፡፡

በአፍሪካ በቆዳ ስፋታቸው ትልቅ ከሚባሉ ሃገራት አንዷ የ100 ሚሊዮን ህዝብ እናት ኢትዮጵያ በአግባቡ አንድ ሚሊዮን እንኳን የማይሞላ ህዝብ ካላት ከጅቡቲ ጋር የዳዊትና ጎሊያድን ያህል ልዩነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ኬንያና ጋናን የመሳሰሉ ቡድኖች በምድቧ ስለነበሩ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ባትችልም የተደራጀና በአግባብ የተያዘ ብሔራዊ ቡድን አላት፡፡ ጅቡቲ ላለፉት ሁለት ዓመታት ብሔራዊ ቡድን እንኳ አልነበራትም፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ከወሰድክ ኢትዮጵያውያን የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ አላችሁ። የኛ ልጆች ተሰብሰበው መዘጋጀት ከጀመሩ ሁለት ወር አልሞላቸውም፡፡ ይህ ውጤት ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአካል ብቃት ልቀን መገኘት ለኛ ቀላል አይደለም፡፡ ከእረፍት መልስ እኛ ሙሉ ለሙሉ በልጠን ነበር፤ ኢትዮጵያውያን ከኛ በባሰ ሁኔታ ደክመው ነበር የቀረቡት፡፡ የግብ ዕድልም በመፍጠር ቢሆን እኛ የተሻልን ነበርን፡፡ ጨዋታውንና ውጤቱን ስታይ ለኛ ውጤቱ አስደሳች ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ጅቡቲን ስትገጥም አምስት ለምንም፣ አራት ለምንም ነበር የምታሸንፈው። አሁን ግን ይሄ ቡድን እንደዚያ አይደለም፡፡

ይህን ብሔራዊ ቡድን የተረከቡት መቼ ነው?

ጥር ወር መጨረሻ ላይ ነው ወደ ጅቡቲ የመጣሁት። የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት የሃገሪቱን ሻምፒዮና ሳስተውል ነበር፤ ተጫዋቾቹን ሰብስቤ ዝግጅት ከጀመርኩ ግን ገና ሁለት ወሬ ነው፡፡ ሃያ ዘጠኝ ተጫዋቾች ከሃገሪቱ ሊግ ይዤ ነው ዝግጅት የጀመርኩት፡፡ ይሄ ቡድን የሁለት ወራት ዝግጅት ውጤት ነው፡፡ ወደፊት ጥሩ ነገር ይታየኛል፡፡

ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ምን ተስፋ ምን ስጋት ተመለከቱ ?

የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጎሎች ያስቆጠሩት ተጫዋቾች የ19 እና የ20 ዓመት ታዳጊዎች ናቸው፡፡ ለብሔራዊ ቡድንም ለመጀመሪያ ጊዜ መጠራታቸው ነው፡፡ ጅቡቲ ላይ ስንጫወት ከተሰለፉት 11 ተጫዋቾች ከግማሽ በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩ ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በታች የሆነ ታዳጊዎች ናቸው፡፡ ይህ ቡድን ከዚህ በላይ የማደግ ተስፋ ያለው ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡

ከጨዋታው በኋላ ስሜትዎ ምን ነበር ?

ክብር.. ኩራት… ቅድም እንደነገርኩህ የቡድናችን አምበል በጉዳት የመልሱን ጨዋታ አላደረገም፡፡ ሌላ የቡድናችን ወሳኝ የመሃል ሜዳ ተጫዋች እሱም በጉዳት የመልሱን ጨዋታ አልተጫወተም፡፡ ዛሬ ቡድናችንን ሲመራ የነበረው አዲሱ አምበል የመጀመሪያዎቹን ሃያና ሃያ አምስት ደቂቃዎች የተቸገረ ይመስል ነበር፣ ነገር ግን እንደገና ወደጨዋታ ተመልሶ ያሳየን ነገር እጅግ የሚያኮራ ነው፡፡ በርግጥ ተጫዋቾቼ ከጨዋታው በኋላ ሜዳ ላይ ሲያለቅሱ ሳይ ሃዘን ተሰምቶኛል፡፡ ማሸነፍ ይገባን ነበር፡፡ ከጨዋታው አንድ ቀን በፊት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሁለት ለዜሮ እናሸንፋለን ብዬ ነበር፣ ጨዋታውን ሳይ ደግሞ በጣም ነው የተቆጨሁት፤ ማሸነፍ ነበረብን፡፡

እኔም ዜናውን አይቼዋለው በጣም ገርሞኝ ነበር ሁለት ለዜሮ እናሸንፋለን ነው ወይስ ከሁለት በላይ አይገባብንም ነው ያሉት?

ሁለት ለዜሮ እናሸንፋለን ነው ያልኩት። አይገባብንም ተብሎ ከተሰራ በጣም ነው የሚገርመኝ። እኔ ሁለት ለባዶ እናሸንፋለን ነው ያልኩት። ምክንያቱም ለማለፍ ሁለት ማግባት ይጠበቅብናል።

ከጨዋታው በኋላ ይህን ወይም ያን ብናረግ የሚል ምናልባት የጸጸት ስሜት?

በፍጹም! በነገራችን ላይ ብዙ ነገር ነው አሸንፈን የወጣነው። 3 ጎል ከሜዳችን ውጭ አግብተናል። ያውም ኢትዮጵያ ላይ ጨዋታ ተቆጣጥረን ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል የጨዋታ ብልጫ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የበለጠ የግብ ዕድል መፍጠር ችለናል። ስለዚህ እኔ ተሸንፈናል ብዬ አላስብም፡፡

ያለደጋፊ መጫወታችሁ ለእንግዳ ቡድን አድቫንቴጅ ነው፤ ያንን አለመጠቀማችሁስ ?

ድሬዳዋና ጅቡቲ ካላቸው ቅርበት የተነሳ የድሬዳዋ ነዋሪ የጅቡቲን ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ተጫዋቾች በላይ ያውቃቸዋል፡፡ ከጅቡቲ የመጡ በርካታ ደጋፊዎች ነበሩን፤ በርካታ ጅቡቲያውያን ድሬዳዋ ይገኛሉ አሁን ደግሞ በተለይ ወቅቱም ክረምት ስለሆነ በሙቀት ምክንያት ድሬዳዋ የሚኖር በርካታ የጅቡቲ ሰው አለ፡፡ ያለህዝብ መጫወታችን ለኛ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ በደጋፊ ፊት ብንጫወት ምናልባት ውጤቱ ሊቀየር ይችል ነበር፡፡

ከጨዋታው በኋላ ለተጫዋቾችዎ ምን አሏቸው ?

አመሰግናለው ነዋ! ምን እላቸዋለው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ገጥማችሁ በሜዳቸው ሦስት ጎል አግብታችኋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን አራትና አምስት አያገቡባችሁም፤ ታሪክ ቀይራችኋል፤ እንኳን ደስ ያላችሁ ነው የምላቸው፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚሉት ካለ?

እንኳን ደስ ያላችሁ። በመጀመሪያው ጨዋታ በሃገራችን መጥታችሁ በማሸነፋችሁ አልፋችኋል። የጨዋታው ህግ በነጥብና በጎል የበለጠ ያልፋል ነው። ስለዚህ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ከዚህም በኋላ መልካም ዕድል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡