“የሊግ ካምፓኒ ምስረታ እንዳይካሄድ ተወስኗል” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

ብዙ ተጠብቆ የነበረውና በስድስት ደቂቃ ውስጥ የተጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሸራተን ሆቴል ዛሬ ያዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለተፉ ይታወቃል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች መካከል ፌዴሬሽኑ በኤሊሊ ሆቴል ያዘጋጀው የሊግ ካምፓኒ ምስረታ አስመልክቶ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የተናገሩት ጉዳይ ነው። የቡናው የቦርድ ፕሬዝዳንት ንግግር እንደሚከተለው ነው፡-

“ትልቁ ቁምነገር እና ችግሮች ይዞ የመጣው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማክሰኞ ሊያደርገው ያሰበው ስብሰባ ነው። እንደምታውቁት አንደኛ የሊግ ካምፓኒ ምስረታው አካሄድ፣ ሁለተኛ የ24 ክለቦች ደግሞ ማቋቋሚያ የሚመስል አካሄዱ ግልፅ አይደለም። ስለዚህ የእኛ ስብሰባ (ጋዜጣዊ መግለጫ) ሲተላለፍ ማክሰኞ ሊካሄድ የታሰበው የሊግ ካምፓኒ ምስረታም እንዳይካሄድ ተወስኗል።

“ሁላችንም እንግዲህ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ባለቤት ሳይሆን (እንደምታውቁት ከፊፋ ጋር የተያያዘ በመሆኑ) እንደ አማካሪ በመሆን አቅጣጫ ያስይዘናል ብለን እንገምታለን። በዚህ አቅጣጫ ውስጥ መንግስት በማንኛውም ጊዜ ሲጠራን ከፊፋ ህግና ደንብ አንፃር በሀገራችን ውስጥ እግርኳስ እንዲያድግ፣ የሊጉንም አመሰራረት በሚመለከት ለመወያየት ዝግጁ ነን፤ ምንም የተዘጋ ነገር የለም። ለማንኛውም እንድታውቁት የምንፈልገው በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተጠራው የማክሰኞ ስብሰባ እንደማይካሄድ ተነግሮናል።”

* በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ከቆይታ በኋላ በገለፀው መሠረት የማክሰኞው የሊግ ካምፓኒ ምስረታ ስብሰባው እንደቀረ ይነገር እንጂ እስካሁን ስለ ቀጣይ የምስረታው እጣ ፈንታ ከፌዴሬሽኑ የተሰጠ መረጃ የለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ