ጅማ አባጅፋር ሁለት ጋናዊ ተጫዋቾችን አስፈረመ

ጅማ አባጅፋሮች ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ እና ተከላካዩ አሌክስ አሙዙን አስፈርመዋል፡፡

ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ ከዚህ ቀደም ለሀገሩ ክለቦች ሚዴአማ እና አሻንቲ ኮቶኮ እንዲሁም ለዛምቢያው ሉሳካ ዳይናሞስ የተጫወተ ሲሆን በጋና ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከዚህ ቀደም መጫወት ችሏል። ባለፈው ክረምት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማምራት ተቃርቦ የነበረውና ዝውውሩ ሳይጠናቀቅ የቀረው ሙንታሪ በጅማ አባ ጅፋር ሁለት ድንቅ የውድድር ዓመታት ያሳለፈው ዳንኤል አጃይን ይተካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የመሐል ተከላካዩ አሌክስ አሙዙ ሌላኛው የክለቡ ፈራሚ ሆኗል፡፡ 2010 በአርባምንጭ ከተማ በመጫወት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር የተዋወቀው ይህ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ዐምና ደግሞ በጣና ሞገዶቹ ቤት ቆይታን ካደረገ በኃላ በባህር ዳር አብሮ መስራት ከቻለው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር በአባ ጅፋር ዳግም ተገናኝቷል፡፡

በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ክለቡ ነገ በተመሳሳይ የጋና ዜግነት ያለው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሊያስፈርም መቃረቡን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ