የ2012 ፕሪምየር ሊግ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ውይይት ተካሄደ

በአዲሱ ዐቢይ ኮሚቴ የሚመራው የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት እና የመተዳደሪያ ደንብ ውይይት ትላንት በአዳማ ኤክስኪውቲቭ ሆቴል ተከናውኗል፡፡

አዲሱ የፕሪምየር ሊግ አመራሮች እና የውድድር ሥነስርአት ኮሚቴ አባላት፣ የክለብ ተወካዮች፣ የፌዴሬሽን ባለሙያዎች እና በእግርኳሱ ውስጥ ያሉ የበላይ አካላት በተገኙበት በአዳማ በተደረገው ውይይት የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር፣ ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በእንግድነት የታደሙበት ሲሆን የፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በመክፈቻ ንግግራቸው ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ተወካዮች በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ከገለፁ በኃላ “የተሳካ የውድድር ዓመት ማሳለፍ እንድንችል ሁሉም በአንድነት ከጎናችን ሊሆን ይገባል።” በማለት በዕለቱ የሚኖሩትን መርሀ ግብሮች በመጠቆም ውይይቱን አስጀምረውታል፡፡

ከሰብሳቢው ንግግር በመቀጠል አዲሱ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉሥ የፕሪምየር ሊጉን የመተዳደሪያ ደንብ ለውይይት ካቀረቡ በኋላ ከእለቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረኩ ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

አስር ምዕራፎች እና ሀያ ሶስት አንቀፆችን ባቀፈው ደንብ አመዛኙ ካለፉት ዓመታት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሲሆን እንደ አዲስ ከተካተቱት ውስጥ በዓመቱ መጨረሻ ወቅቶች የውዝግብ መነሻ ሲሆኑ የሚታዩት በተመሳሳይ ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎችን በተመለከተ በአንደኛው ሜዳ መቋረጥ ከገጠመ ሁሉም በተመሳሳይ ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ይቋረጣሉ፤ በተጨማሪም ለመቋረጡ ምክንያት የነበረው አካል የገንዘብ ቅጣት ይተላለፍበታል፤ በወቅቱ ወጥተው ለነበሩ ወጪዎች ማስፈፀሚያም ይውላል የሚለው ተጠቅሷል።

ሌላው ከፕሪምየር ሊጉ በወቅቱ አለመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አጨቃጫቂ ጉዳይ የተጫዋቾች ውል ነው። የተጫዋቾች ውል 30 እንደሚጠናቀቅ የሚታወቅ ሲሆን እስከ ሰኔ 15 ይጠናቀቃል የተባለው ሊጉ በተለያዩ ምክንያቶች ሰኔ 30 የሚሻገር ከሆነ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ተጫዋቾች ከውላቸው ውጪ ክለቦችን የማገልገል ግዴታ እንዳለባቸው ተጠቅሷል።

ከብሔራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ ዋሊያዎቹ ጨዋታ በሚኖራቸው ወቅት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እንደማይኖሩ ሲገለፅ በደንቡ ላይ ከተካተቱ ሌሎች ህግጋት መካከል በጥሎ ማለፉ ላይ ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የመሳተፍ ግዴታ እንዳለባቸውና ይህን በማይፈፅም ክለብ ላይ 150 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልበት ቢካተትም በውይይቱ ላይ ጥሎ ማለፉ በዚህ ዓመት እንደማይካሄድ ከስምምነት በመደረሱ ከዚዝ ውድድር ጋር ተያያዙ ደንቦች ሊሻሩ ችለዋል።

ከደንቡ በተጨማሪ ሌሎች ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ደንቡ ላይ ከተጠቀሱት መካከል ከህግ እና ፍትህ አወሳሰን ወይንም አሰጣጥ ላይ የተነሱት ሀሳቦች በአንድ ቀን ስብሰባ የሚተገበሩ ሳይሆኑ ራሱን የቻለ የግንዛቤ ስልጠና ያስፈልገዋል፤ ሊጉ የራሱ ሎጎ እና የሥያሜ ስፖንሰር ቢኖረው የሚሉት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

ከመድረኩ በተነሱት አስተያየት እና ጥያቄዎች ላይ በተለይ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ምላሽ ሰጥተዋል። “ሊጉ ራሱን የቻለ ሎጎ እንዲኖረው ጥረት እያደረግን ነው። ለጊዜው ግን የፌዴሬሽኑን አርማ እየተጠቀምን የምንቀጥልበት ይሆናል። የሊጉ መጠሪያ ስፖንሰርን በተመለከተም ድርጅቶች እና ተቋማት እግርኳሱን ወደ ሰላም መመለስ ካልቻላችሁ ስፖንሰር መሆን አንችልም ብለውናል። እናንተም ይህን በመረዳት እግር ኳሳችንን ማከም አለብን። ያን ካደረግን መፍትሔው በእጃችን ነው።” ብለዋል፡፡ ሰብሳቢው ጨምረውም “ከህግ እና ፍትህ አወሳሰን ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጥያቄ ተቀብለናል። ባላችሁን መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት ተዘጋጅተናል።” ያሉ ሲሆን ለዚህም ደግሞ ሁሉም ከጎናችን መቆም አለበት ብለዋል፡፡

በዕለቱ የዳኛ እና የኮሚሽነሮችን ሥም ፌድሬሽኑ መልምሎ ለኮሚቴው ያቀረበ ሲሆን የምደባው ሂደትም በአዲሱ የውድድር እና ስነስርአት ኮሚቴም ተፈፃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ባለፈ የክለብ ምዝገባ እና የዳኞች ክፍያን አዲስ በወጣው የባንክ አካውንት እስከ ውድድሩ ጅማሮ ድረስ ፈፅመው እንዲጨርሱ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በሰተመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እንደ ፌዴሬሽን ከዚህ ኮሚቴ አጠገብ በመሆን ክትትል እንደሚያደርጉ ቃል ከገቡ በኃላ የዕጣ ማውጣት ስነስርአቱ ተከናወኖ ተፈፅሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ