ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በዚህ ሳምንት በአዲስ በአበባ ስታዲየም በብቸኝነት የሚካሄደውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ሰበታ ከተማዎች የሚጠቀሙበት ስታዲየም ብቁ አለመሆኑን ተከትሎ ለውጥ ለማድረድ በመገደዳቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄደው ይህ ጨዋታ ሁለት የተለያየ አቀራረብ ያላቸው እና እቅድ ያለው አጨዋወት የሚከተሉ ቡድኖች የሚያገናኝ እንደመሆኑ ተጠባቂ የሜዳ ፍልሚያ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሰበታ ከተማን ይዘው አዲስ ቡድን በመገንባት በአዲስ አባባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተፎካካሪ ቡድን ያሳዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ምንም እንኳ በለውጥ ሂደት ላይ ያለ ቡድን ይዘው ጠጣር የመከላከል አጨዋወት የሚከተልን ቡድን ቢገጥሙም ቡድኑ በአዲስ አበባ ዋንጫ ባሳየው ጥሩ አቋም ቀላል ግምት አይሰጣቸውም።
እንደተጋጣምያቸው ሁሉ በዝውውሩ በርካታ ዝውውሮች የፈፀሙት ሰበታዎች በመስኮቱ ያዘዋወሯቸው ተጫዋቾች በአሰላለፋቸው ላይ ያካትታሉ ተብለው ሲጠበቁ በብሄራዊ ቡድን ጉዳት ያስተናገደው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ ክለቡን አያገለግልም።

የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በመሳተፍ ያሳለፉት ወልዋሎዎች በውድድሩ ባለፈው ዓመት ከታዳጊ ቡድን ካደጉት ሽሻይ መዝገቦ፣ ሰመረ ሃፍታይ ፣ ስምዖን ማሩ እና ግብ ጠባቂው ዓብዱልዓዚዝ ኬታ ውጭ በአዲስ የተጫዋቾች ስብስብ ነው ለሊጉ የሚቀርቡት። በአዲስ አበባው ውድድር ከተጋጣሚያቸው ሰበታ ከተማ ጋር ተገናኝተው የነበሩት ወልዋሎዎች በውድድሩ በርካታ ክፍተቶች ቢታይባቸውም ለዚህ ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብ ይዘው ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው ዐቢይ ጉዳይ በውድድሩ በህመም ምክንያት የአሰልጣኛቸው ዮሐንስ ሳህሌ ግልጋሎት ማግኘታቸውና አሰልጣኙ በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች በጥንቃቄ እና መከላከል ላይ ላመዘነ አጨዋወት የሚሰጡት ትኩረት ነው።

ወልዋሎዎች በዚህ ጨዋታ በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታ

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።

– በቅርቡ በተጠናቀቀው የአአ ከተማ ዋንጫ በአንድ ምድብ ተደልድለው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ሰበታ ከተማ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል።

– ሰበታ ከተማ በ2003 ሰኔ ወር ላይ ሀረር ቢራን 2-0 ካሸነፈበት ጨዋታ 8 ዓመታት በኋላ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን ያከናውናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ፍርዳወቅ ሲሳይ – አዲስ ተስፋዬ – ሳቪዮ ካቩጎ – ጌቱ ኃይለማርያም

መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ታደለ መንገሻ

ኢብራሂም ከድር – ባኑ ዲያዋራ – በኃይሉ አሰፋ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ

ገናናው ረጋሳ – ዓይናለም ኃይለ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሐንስ

አቼምፖንግ አሞስ – ካርሎስ ዳምጠው

ራምኬል ሎክ – ሚካኤል ለማ – ኢታሙና ኬሙይኔ

ጁንያስ ናንጂቦ


© ሶከር ኢትዮጵያ