የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 3-1 ጅማ አባጅፋር

የ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር መክፈቻ ከሆነው የሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

👉 “በአጠቃላይ ቡድኔ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት መሻሻሎችን እየተመለከትኩ ነው” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ለእኛ ጨዋታው መጥፎ አልነበረም። ከጨዋታው በፊት ጅማዎች በጣም ወደ ሜዳቸው አፈግፍገው ይጫወታሉ ብለን ነበር አስበን የመጣነው። ለዚህም ደግሞ በደንብ ተዘጋጅተን ነበር። በጨዋታውም የገጠመን የጠበቅነው ነው። እነሱ ትንሽ ወጣ ብለው ለመጫወት የሞከሩት ከጎሉ በኋላ ነው። ባለፈው ጨዋታ ከሜዳችን ውጪ ተሸንፈን ስለመጣን እና ዛሬ አሸንፈን ወደ አሸናፊነት ስለ ልቦና ስለተመለስን ትልቅ ነገር ነው። በአጠቃላይ ቡድኔ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት መሻሻሎችን እየተመለከትኩ ነው።

ስለ ቡድኑ የመስመር አጨዋወት

ኳስ መቆጣጠር የምትፈልግ ከሆነ በሜዳ ላይ ያሉት ሁሉም ተጫዋቾች በእንቅስቃሴ መሳተፍ አለባቸው። የመስመር ተከላካዮችህ ደግሞ በማጥቃቱ ላይ የሚሳተፉ ከሆነ ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ትችላለህ። ይህ ብቻ ሳይሆን ኳሱ ከእግርህ ሳይወጣ ብልጫ መውሰድም ትችላለህ። ዛሬም ታታሪው ጌቱን አስቀምጠን ኢብራሂምን የተጠቀምነው ኳስን በደንብ ለመቆጣጠር በማሰብ ነው። ጌቱ መሮጫ ቦታዎችን በእንቅስቃሴ ስለሚፈልግ እና ተጋጣሚያችን ጅማዎች ደግሞ የመሮጫ ቦታዎችን እንደሚነፍጉን በማሰብ ከኳስ ጋር ጥሩ የሆነው ኢብራሂምን አስገብተናል። ወደፊትም እንደየተጋጣሚያችን አቀራረባችንን ለመቃኘት እንሞክራለን።

ስለ ቡድኑ የራስ መተማመን

ማንኛውም ዓይነት ተጫዋች ቢኖርህ ሥነ ልቦና ከሌለህ ዋጋ የለውም። በእንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በሥነ ልቦናውን ረገድ ከእለት ወደ እለት መሻሻሎች አሉ። ባለፉት ጨዋታዎች ቡድኔ ኳስ ከኋላ ለመጀመር ፍራቻ ይስተዋልበት ነበር። አሁን ይህንን ልናስወግድ ችለናል። ከዚህ በተጨማሪም ከግብ ጠባቂያችን ዳንኤል አጃይ የሚለጉ ረጃጅም ኳሶችን ቀንሰናል። እነዚህ ነገሮች በስነልቦናው እንደተሻሻልን የሚያሳዩ ናቸው። ሁሉም ጨዋታዎች ለእኛ ከሜዳችን ውጪ ናቸው። አዲስ አበባ ስታዲየምም የእኛ ሜዳ አደለም። በአጠቃላይ በሽሬ ከተሸነፍንበት ጨዋታ ውጪ ምንም መጥፎ ውጤት ከሜዳችን ውጪ የለም።

👉 “ከ16ቱ የሊጉ ክለቦች 72 ሰዓታት ሳያርፍ ቀጣይ ጨዋታ ያደረግነው እኛ ብቻ ነን” ጻውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባ ጅፋር)

ጨዋታውን እንዴት አገኘኸው?

መጀመሪያ ተጋጣሚያችንን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ከ16ቱ የሊጉ ክለቦች 72 ሰዓታት ሳያርፍ ቀጣይ ጨዋታ ያደረገው ክለብ የኛ ክለብ ብቻ ነው። ተጋጣሚያችን ደግሞ 96 ሰዓታት አርፈው ነው ለጨዋታው የቀረቡት። በህጉ መሰረት ደግሞ አንድ ክለብ 72 ሰዓት ማረፍ አለበት። ስለዚህ በህጉ መሰረት ይህንን ጨዋታ እኛ ማድረግ አይገባምን ነበር። ተጨዋቾቼ በጣም ደክመው ነበር። ከጊዮርጊሱ ጨዋታ ጀምሮ በአዳማው እና በወልቂጤው ጨዋታ ብዙ ጉልበት አፍስሰን ነበር። አዲስ አበባም ከገባን በኋላ ጥሩ የልምምድ ሜዳ አላገኘንም ነበር። ስለዚህ በጣም ተዳክመው ነበር። በአጠቃላይ በእንቅስቃሴ ደረጃ ብዙም የሚያስከፍ ነገር የለም ግን ተጨዋቾቼ አጥቅተው ለመመለስ ሲደክሙ አይቻለሁ። ውጤቱን እኔ እና ተጫዋቾቼ በፀጋ ተቀብለነዋል።

መርሐ ግብሩን ለምን አላስቀየራችሁም?

በሥራ አስኪያጃችን በኩል ጥያቄ አቅርበን ነበር። ነገ ሜዳው ተይዟል ተብሎ እንደዚህ አይደረግም። እኛ ምንም ማድረግ ስለማንችል መጥተን ተጫውተናል። ነገ 9 እና 11 ሰዓት ማጫወት ይችሉ ነበር። 70 ሰዓታትን ብቻ አርፈን መጫወት የለብንም። እንደገለፅኩት ተጋጣሚያችን ከእኛ 1 ቀን አርፎ ነው የመጣው። ይህ ስለተሸነፍን እንደምክንያትነት እያቀረብኩት አይደለም። ግን ህጉ ለሁሉም በአሁኑ እኩል መተግበር አለበት። በቀጣይ ግን ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚፈለገውን ሥራ እንሰራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ