ቅድመ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ስሑል ሽረዎች አዲስ አዳጊዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎችን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባለፈው ሳምንት ወደ ድሬዳዋ አቅንተው ከብርቱካናማዎቹ ጋር ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት ስሑል ሽረዎች ከመሪዎቹ ላለመራቅ ማሸነፍን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ

በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት ሽረዎች በነገው ጨዋታም ከተለመደው የራቀ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠቅም። ሆኖም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በሁለቱም መስመሮች ተመሳሳይ ሚዛን ያለው የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት የቀድሞ አስፈሪነቱን ለመመለስ እና በተጋጣሚ ተገማች ላለመሆን በቀኝ መስመር ላይ ለአጨዋወቱ የሚሆን ሁነኛ ተተኪ ማሰለፍ ይጠበቅበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት ወንድወሰን አሸናፊን በቀይ ካርድ አጥተው በሦስተኛ ተመራጭ ግብ ጠባቂያቸው ዋልታ ዓንደይ ጨዋታውን ለመጨረስ የተገደዱት ሽረዎች ምንተስኖት አሎ ከቱርክ መመለሱ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።

ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ ምንተስኖት አሎን ወደ አሰላለፉ ይመልሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ወንድወሰን አሸናፊ እና ዲዲዬ ለብሪን በቅጣት አያሰልፉም። ዮናስ ግርማይም በጉዳት ቡድኑን የማያገለግል ተጫዋች ነው።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ

ባለፈው ሳምንት በፀጋዬ ኪዳነማርያም ስር የመጀመርያው ጨዋታቸውን አድርገው በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ነብሮቹ ይህ ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ወሳኝነት አለው።

በመጀመርያው ጨዋታቸው ከቀደመው የቡድኑ አጨዋወት ብዙም ለውጥ ለማድረግ ያልደፈሩት አዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ በዚ ጨዋታ ይዘውት የሚገቡትን አጨዋወት ለመገመት ቢከብድም የቡድኑን ደካማ የተከላካይ መስመር በማጥበቅ ለተጋጣሚ መልሶ ማጥቃት የተለየ ዝግጅት ማድረጉ አይቀሬ ነው። በአብዛኞቹ የሊግ ጨዋታዎች እንደታየው በቢስማርክ አፕያ እና ቢስማርክ አፓንግ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት ይኖራቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ሆሳዕናዎች በሁለቱ የቀድሞ ቡድናቸው የሚገኘሙት ጋናውያን አጥቂዎች ብዙ ተስፋ ጥለው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ቡድኑ ጨዋታው ከሜዳው ውጭ እንደመሆኑ አሉታዊ የሆነ አቀራረብ ይዞ ካልገባም አማካዮቹ ይሁን እንደሻው እና አፈወርቅ ኃይሉ በማጥቃቱ ላይ ጥሩ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በነገው ጨዋታ ዓብዱልሰመድ ዓሊን በጉዳት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

የነገው ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙበት ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ዓወት ገብረሚካኤል – አዳም ማሳላቺ – በረከት ተሰማ – ረመዳን የሱፍ

ነፃነት ገብረመድህን – ሀብታሙ ሽዋለም

ክፍሎም ገብረህይወት – ያስር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ

ሳሊፍ ፎፋና

ሀዲያ ሆሳዕና (4-4-2)

አቤር ኦቮኖ

ፀጋሰው ዴማሞ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ – ሄኖክ አርፊጮ

ሱራፌል ዳንኤል – ይሁን እንዳሻው- አፈወርቅ ኃይሉ – በኃይሉ ተሻገር

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

©ሶከር ኢትዮጵያ