መቐለ 70 እንደርታ ለወረርሺኙ መከላከያ ድጋፍ አድርጓል

የመቐለ 70 እንደርታ እግርኳስ ክለብ፣ የሴት እና የወንድ ቡድን ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ድጋፍ አድርገዋል።

በወቅቱ አስጊ ደረጃ ላይ ለደረሰው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የበርካታ ሰው ሕይወትን የቀጠፈው የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል በእግር ኳስ ቤተሰቡ በኩል በርካታ ድጋፎች መደረጋቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታዎች ከአራቱም ቡድኖቻቸው የተውጣጣ የስድስት መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድርገዋል። በዚህም የወንድ እና የሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ግማሽ ደሞዛቸውን ሲለግሱ የእጅ ኳስ ተጫዋቾች አስር ሺ አራት መቶ ብር እንዲሁም የብስክሌት ቡድናቸው አስራ ሁለት ሺ ብር እና የደጋፊ ማሕበሩ አስር ሺ ብር እንደለገሱ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በግላቸው የሀምሳ ሺ ብር ድጋፍ ሲያደርጉ የተቀሩት የአሰልጣኞች ቡድን አባላትም የዋናው አሰልጣኙ መንገድ ተከትለው ድጋፍ አድርገዋል።

ቡድኑ በትናንትናው ዕለት ከቦርድ አመራሮች እና ከደጋፊ ማኅበር አመራሮች ጋር በመሆን በእንደርታ ወረዳ የምትገኝ አንዲት የገጠር ሰፈር በማምራት በግምት አስር ሺ ብር የሚያወጣ የንፅህና መጠበቅያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ወደ ስፍራው ያመራው የቡድኑ ልኡካን ቡድን ከቁሳቁሱ በተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም እንደሰራ ከቡድኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከዚ ቀደም በቡድኑ የሚገኙት አንተነህ ገብረክርስቶስ ፣ሶፈንያስ ሰይፈ ፣ ያሬድ ከበደ፣ ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ ምሕረትአብ ገብረህይወት እና አሸናፊ ሀፍቱ በግላቸው ድጋፎች ማድረጋቸው ይታወሳል። የሴት ቡድኑ አሰልጣኝ ህይወት አረፋይነም በግሏ ለአረጋውያን ድጋፍ ማድረጓ አይዘነጋም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: