የሴቶች ገፅ | ወርቃማዋ እንስት ሽታዬ ሲሳይ

በቡድን ስኬት እና በግል ክብሮች ባንፀባረቀው የእግር ኳስ ህይወቷ ከትምህርት ቤት ተነስታ እስከ ብሔራዊ ቡድን የዘለቀችው ሽታዬ ሲሳይን የዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን በስፋት ተመልክቷታል፡፡

ኳስን የጀመረችው ተወልዳ ባደገችበት አዲስ አበባ አዲሱ ገበያ አካባቢ ከወንድ ጓደኞቿ ጋር በመጫወት ነበር። ስኬታማዋ አጥቂ ሽታዬ ሲሳይ አባቷ ከኳሱ ይልቅ ትምህርቷ ላይ ብቻ እንድታተኩር በተደጋጋሚ ይገስጿት ስለነበር የልጅነት ዕድሜዋን በፕሮጀክት ደረጃ ለመጫወት አልታደለችም። የያኔዋ ታዳጊ የአባቷን ምክር እየዘነጋች ሱቅም ቢሆን በተላከችበት ቅፅበት ሁሉ የሠፈሯ ልጆች ኳስ ሲጫወቱ ስታይ ገብታ ትጫወታለች። ሁልጊዜ ከተላከችበት እየዘገየች ስትመጣም አባቷ በመጠራጠር ክትትል ይጀምራሉ። በእግር ኳስ ፍቅር የተለከፈችው አጥቂ ግን አሁንም የአባቷን ‘ተማሪ’ የሚል ድምፅ እየዘነጋች መጫወቷን ቀጠለች። የአባቷም ግሳፄ ዱላንም ጭምር ቢያካትት እንኳን እሷ ግን አሁንም መጫወት አላቆመችም። ሠፈር ውስጥ ክልከላው ቢበዛባትም ትምህርት ቤት ውስጥ መጫወቷ አልቀረም። ዛሬ ላይ አብራት በንግድ ባንክ የምትጫወተው ታናሽ እህቷ ብዙነሽ ሲሳይ ትምህርት ቤት ኳስ እየተጫወተች መሆኗን ለአባታቸው ነግራባት ቁጣው እና ግሰፃው ቢቀጥልም ከኳስ የሚለያት አልሆነም።

በኳስ ፍቅር ይህን ፈታኝ የልጅነት ጊዜ ያሳለፈችው ሽታዬ ከሠፈር ይልቅ በትምህርት ቤት በምታሳየው እንቅስቃሴ የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ በተለያዩ ክለቦች ተፈላጊነቷ እየጨመረ መጣ። “ትምህርት ቤት ስጫወት አለባቸው ተካ (አለቤ) የሚባል ቡድን ፈለገኝ። የቡድኑ አሰልጣኝ ፍቃዱ ማሞ (ባቢ) ለትምህርት ቤት ስጫወት መጥቶ አየኝ እና እሱ ጋር እንድጫወት ጠየቀኝ። በአጋጣሚ እኔ እና የአሁኗ ግብ ጠባቂ ማርታ በቀለ አብረን ነበር ለትምህርት ቤት የምንጫወተው። እሷ በሰዓቱ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን በሆነው የካ ክፍለ ከተማ ትሰራም ነበር፡፡ ‘ የእኛ ቡድን ቆንጆ ነው ፤ እዚህ ብትገቢ ጥሩ ነው’ ብላኝ ወደ አሰልጣኝ ብርሀኑ ጋር ወሰደቺኝ።” ስትል ጅምሯን በየካ እና አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ስር እንዳደረገች ትናገራለች።

የካ ለሽታዬ መንደርደሪያዋ እንጂ ከክፍያ አንፃር ይህ ነው የሚባል ጥቅምን የምታገኝበት አልነበረም፡፡ልጅ ከመሆኗ አንፃርም ለትራንስፖርትም ሆነ ለኪሷ የሚሆን ገንዘብ ይቸግራት የነበረ በመሆኑ አሰልጣኟ ብርሀኑ ትልቅ ደረጃ ደርሳ ሊመለከታት ይመኝ ስለነበር ከኪሱ እገዛ ያደርግላት ነበር። እሷም ይህን በመረዳት ራሷን በሂደት እየገነባች መምጣት ቻለች። “አሰልጣኝ ብርሀኑ ጋር በገባሁበት ጊዜ የነበረው ነገር ደስ ይላል በጣም ጎበዝ እና ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችም ነበሩ፡፡ ማርታ ከእሱ ጋር አስተዋወቀቺኝ። አስራ አምስት ቀናትን ያህል እየተቸገርኩ መጫወት ጀመርኩ። ከዚያ በኃላ ግን የትራንስፖርት ስላልነበረኝ ቀረውኝ። ቢሆንም ብርሀኑ የቸገረኝን እንደሚያግዘኝ ነገረኝ ፤ የትራንስፖርትም እየሰጠኝ መስራት ቀጠልኩ።” ስትል የአሰልጣኟን ውለታ ታስታውሳለች። በዚህ ቡድን ውስጥ ራሷን በሚገባ እያበሰለች የመጣችው ሽታዬ ከየካ በተጨማሪ በለጋ ዕድሜዋ ለአዲስ አበባ ምርጥ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ጭምር የመጫወትን ዕድል አግኝታለች፡፡ በተለይ አዲስ አበባን ወክላ መቐለ ላይ በነበረው ውድድር በግሏ የኮከብ ግብ አግቢነትን ክብርን በመጎናፀፏ ኳስን አጥብቀው ሲከለክሏት የነበሩት አባቷ በቴሌቪዥን ስትሸለም ሲያዩ እጅጉን ደስተኛ ከመሆናቸው ባለፈ መልካም እንዲገጥማት ምኞታቸውን ገልፀውላታል። ምንም እንኳን አባቷ በሞት ቢለይዋትም የምርቃታቸው በረከት ደርሷት በትልቅ ደረጃ በመጫወት ለቤተሰቧ ኩራት መሆን ችላለች።

ከ1995-1997 ድረስ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ስር በየካ ክፍለ ከተማ የተጫወተችው ሽታዬ በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርታ ለአራት ዓመታት ቆይታለች፡፡ በቡና ሳለች ወደ 204 ግቦችን ከመረብ እንዳሳረፈች የምትገልፀው ሽታዬ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዲቪዚዮን በሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ ውስጥ በዲቪዚዮኑ እና በጥሎ ማለፍ ውድድር በድምሩ ስምንት ዋንጫዎችን ከቡድን አጋሮቿ ጋር አሳክታለች፡፡ በቤተሰቧ ጫና ቢደርስባትም ምንም ነገሮች ከመንገዷ ሊያግዷት ያልቻሉት አጥቂዋ ከቡናማዎቹ ጋር ከተለያየች በኃላ የልጅነት አሰልጣኟ ብርሀኑ ግዛውን ጥሪ ተከትላ በሚሊኒየሙ ወደ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ በማምራት ለሦስት ዓመታት ተጫውታለች። ከጎል ጋር የጠበቀ ትውውቅ ያላት እንስቷ እንደሷ አገላለፅ በዚህ ቡድን ውስጥም ሰባት ዋንጫዎችን ከማግኘቷ በተጨማሪ አንድ መቶ ስልሳ ስምንት ግቦችን ከመረብ አዋህዳለች። በዚያን ወቅት ከሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ጎን ለጎን አዲስ አበባን ወክላ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይም ተሳትፋለች።

በሴንትራል እጅግ መልካም ዓመታትን ያሳለፈችሁ አጥቂዋ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ 2003 ላይ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሸጡን ተከትሎ እሷም አብራ ተዘዋውራለች፡፡ በንግድ ባንክም ብዙሀኑ የስፖርት አፍቃሪ ይበልጥ እያወቃት መጣ። ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታዋ ያሸረበረቁ ወርቃማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችላለች፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 2004 ላይ ሲጀመር ሽታዬ በየሚዲያው ስሟ በተደጋጋሚ መጠራት ጀመረ። ግብ አግቢነቷ ፣ ቅልጥፍናዋ እና አብዶኝነቷ የምታስቆጥራቸው ግሩም ግቦችም የእሷነቷ መለያዎች እየሆኑ መጡ። “እግዚአብሔርም ሲፈጥረኝም በተፈጥሮ አድሎኛል። ብዙውን ለውጥ ያመጣውት ግን ብርሀኑ ጋር ነው። በደንብ ያሰራኛል ፤ ያው ድፍረቱም አለ አቅምም አለኝ ብዬ ስለማስብ ጎል አግቢም ስለሆንኩኝ የማግባት ሂደት ውስጥ አልጠፋም።” የምትለው ሽታዬ ከ2004 ጀምሮ በባንክ ቆይታዋ ከፕሪምየር ሊግ እስከ ጥሎ ማለፍ አስር ዋንጫዎችን ስታሳካ መቶ ሀምሳ አራት ግቦችን ከመረብ ማገናኘቷንም ትገልፃለች። በ2005 ኮከብ ተጫዋች ፣ በ2006 ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች ፣ በ2007 ደግሞ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመባል ተሸልማለች። በሠፈር ውስጥ የክረምት ውድድር ከብራዚል የመለያ ሽልማት የጀመረው ስኬቷ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በሊጉ ሽልማቶች በትልቁ ደምቆ ታይቷል።

ከእነዚህ አስደሳች ዓመታት በኋላ ግን 2009 ለተጫዋቿ ጥሩ ነገርን ይዞ አልመጣም። ጉልበቷ ላይ ከበድ ያለ ጉዳት በማስተናገዷ ለሁለት ዓመታት ከሜዳ ለመራቅ ተገዳለች። በክለቧ ንግድ ባንክ ወጪም ጉልበቷ ላይ ቀዶ ህክምና ከተደረገ በኃላ አምና ዳግም ወደምትወደው እግር ኳስ ተመልሳለች። ” ጉልበቴን ሰርጀሪ ተሰርቻለሁ። ከጉዳት በኋላ ወደ በፊቱ አቋም ለመመለስ ትንሽ ይከብዳል። ከህመሙ እና ከጫናው በተጨማሪ ጊዜም ይፈልጋል። እኔም እስካገግም ጊዜ ፈጅቶብኛል። 2009 እና 2010 ብዙም አልተጫወትኩም። አሁን ግን እየተሻለኝ በመሆኑ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻልኩ መጥቻለሁ።” በማለት ስለከባዱ ጊዜ ትናገራለች።

ያኔ በጨቅላ ዕድሜዋ እንዳትቸገር እና እግር ኳስን አጥብቃ እንድትይዝ ሲደጉማት እንዲሁም አባቷን ቤት ድረስ በመሄድ ኳስን እንድትጫወት ሲማፀንላት የነበረው አሰልጣኝ ብርሀኑ ዛሬ ላይ ከአሰልጣኝነትም በላይ ቤተሰቧም ነው ፤ የሁለት ልጆቹ የክርስትና እናትም ሆናለች። “ሽታዬን ያገኘዋት በጣም በህፃንነቷ ነው። ስራዋን በጣም የምትወድ እና ብዙ የማታወራ ሜዳ ላይ በእግሯ ብቻ የምትናገር ነበረች። ስራዋ በራሱ ያወራል። ከሜዳ ውጪ ደግሞ በጣም ዝምተኛ ነበረች። በጊዜ ሂደት ግን ኳሱም እየገባት እየዳበረች መጥታ ኃይለኛ ሆናለች። አሁን ሽታዬ ካለች ለየትኛዋም ከሷ ጋር ላለች ተጫዋች ፈገግታን ትጨምራለች ፤ ማታመጣው ጨዋታ የለም። በጣም ትጉ እና ቅን እግር ኳስን የምትወድ እና ለኳስ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለች ልጅ ናት።” ሲል ለዓመታት አብሯት የሰራው አሰልጣኟ ይገልፃታል፡፡

ከልጅነት ጊዜዋ ከ1996 ጀምሮ ዛሬም ድረስ በሉሲዎቹ ስብስብ ውስጥ የማትጠፋው ሽታዬ ሲሳይ ረጅም ዓመታትን በተለያዩ ክፍለ አህጉራዊ አህጉራዊ ጨዋታዎች ላይ ብትካፈልም የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ቁጭት እንዳለባት ትጠቁማለች። “ብሔራዊ ቡድን በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ። ግን ያለፉት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ማለፍ አለመቻላችን በጣም ይቆጨኛል። ከዚህ በፊት ያገኘነው አጋጣሚ ጥሩ ነበር። ለአፍሪካ ዋንጫ በድጋሚ ማለፍ አለመቻላችን ግን ያብከነክነኛል። ብንችል በቀጣይ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድል እንዲኖረን እፈልጋለሁ። እነዚህን እስከ አሁን አለማሳካታችን ይቆጨኛል” ብላለች፡፡

ሽታዬ ከታናሽ እህቷ ብዙነሽ ሲሳይ ጋር

አምስት እህቶች እና አንድ ወንድም ያላት ሽታዬ አባቷ በህይወት ቆይተው አሁን የደረሰችበትን አለማየታቸው ቢቆጫትም የእሷን ፈለግ ከተከተለችው ከታናሽ እህቷ ብዙነሽ ጋር በስኬት መዝለቋ አልፎም ደግሞ በንግድ ባንክ አብራት መጫወቷ እንደሚያስደስታት ትገልፃለች፡፡ በጓደኞቿ ዘንድ ተጫዋች እና ቀልደኛ በሜዳ ላይ ደግሞ አልሸነፍ ባይ እንደሆነች የሚነገርላት አጥቂዋ በኢትዮጵያ ቡና ስትጫወት የቡድን አጋሯ የነበረችሁ የአሁኗ የአዳማ ተከላካይ ወይንሸት ፀጋዬ (ኦሎምቤ) ቡድን በማረጋጋት ተሰጥኦዋ ‘ሽቱ በረዶ’ የሚል ቅፅል ስም አውጥታላት እስካሁንም መጠሪያዋ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ከ199ዎቹ አጋማሽ እስከ አሁን ስኬት ያልተለያት ‘ሽቱ በረዶ’ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ አልፋ በእግር ኳስ ህይወቷ ጠንክራ በመግፋቷ ዛሬ ላይ የግል ቤት እና መኪና ባለቤት ናት፡፡ በእግር ኳስ ህይወቷ 29 ዋንጫዎችን የሳመችው አብዶኛዋ አጥቂ እንደራሷ እና ብርሀኑ ግዛው ሀሳብ ከሆነ ወደ 588 ግቦችን ከመረብ አሳርፋለች፡፡ እዚህ ለመድሯሷ ትልቅ ድጋፍ ላደረጉላት ምስጋናዋን ስትቸር “በመጀመሪያ ለዚህ ያበቃኝ ፈጣሪ አምላክን ማመስገን እፈልጋለሁ። ሲቀጥል ብርሀኑ ግዛውን በጣም ነው የማመሰግነው። እኔ ባለኝ አቅም ብቻ ሳይሆን ብዙውን ነገር ያደረገልኝ እሱ ስለሆነ በጣም አመሰግነዋለሁ። እንደገና ሠፈር ውስጥ ስጫወት እገዛ ያደርግልኝ የነበረው ደምሰው ፍቃዱንም ማመስገን እፈልጋለው። ” በማለት ሀሳቧን ቋጭታለች፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ