ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው ሳምንት የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታው ከወልቂጤ ከተማ ጋር ሁለት አቻ የተለያየ ሲሆን የመሐል እና የመከላከል ክፍሉን ለማጠናከር ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ፡፡

በመከላከያ ያለፉት ሦስት ዓመታት ሲጫወት የቆየው የመሐል ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ ከወራት በፊት ክለቡን ለቆ ወደ መቐለ ያመራ ቢሆንም ክለቡ በሊጉ መሳተፍ ስለማይችል ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከሰሞኑ ልምምድ ሲሰራ ቆይቶ በአንድ ዓመት ውል ክለቡን ዛሬ ተቀላቅሏል፡፡

ሁለተኛው ፈራሚ ተስፈኛው አማካይ ዊሊያም ሰለሞን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተገኘው እና በእግር ኳስ ህይወቱ ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፈው ይህ ወጣት ባለፈው ዓመት በመከላከያ አስደናቂ ጊዜ አሳልፎ ከቆየ በኃላ ማረፊያውን በአራት ዓመት ውል ቡናማዎቹን አድርጓል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ