ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያዎቹ፣ ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቅዳሜ እስከ ሰኞ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል። በጅማሮው ላይ የተከሰቱ የመጀመርያ ክስተቶች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎች የሚከተሉት ናቸው።


የመጀመርያዎቹ

– የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ በሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል ተካሂዶ ያለ ጎል ተጠናቋል። ኢንተርናሽናል አርቢቴር በላይ ታደሰም የመጀመርያውን የማስጀመርያ ፊሽካ አሰምተዋል።

– የሊጉ የመጀመርያ ጎል በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ተቆጥሯል። የፋሲል ከነማው አጥቂ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን በረታበት የመጀመርያው ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በ 44ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ጎሉን ያስቆጠረው።

– አስጨናቂ ሉቃስ የመጀመርያው የቢጫ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች ነው። የድሬዳዋ ከተማው አማካይ በመክፈቻው ጨዋታ ደቂቃ ላይ በሰራው ጥፋት በበላይ ታደሰ ካርድ ተመዞበታል።

– የመጀመርያው የቀይ ካርድ በጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ላይ ተመዟል። ወጣቱ ግብ ጠባቂ ከአዳማ ጋር በተደረገው ጨዋታ ገና በስምንተኛው ደቂቃ ላይ ከጎል ክልሉ ወጥቶ በሰራው ጥፋት ነበር የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው።

– የመጀመርያው የፍፁም ቅጣት ምት ድሬዳዋ ከተማዎች ከሰበታ ባደረጉት ጨዋታ 38ኛ ደቂቃ ላይ ቢያገኙም ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል መትቶ በፋሲል ገብረሚካኤል ሲመክንበት በሁለተኛው ቀን በተደረገው የቡና እና ወልቂጤ ጨዋታ በ50ኛው ደቂቃ የመጀመርያው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በአቡበከር ናስር አማካኝነት ተመዝግቧል።

– በጨዋታ ከአንድ በላይ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻለው የቡናው አቡበከር ናስር ነው። አጥቂው ወልቂጤ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል። ታፈሰ ሰርካ፣ አብዲሳ ጀማል እና ፍፁም ዓለሙ ሌሎች የሁለት ጎል ባለቤቶች ናቸው።

የሳምንቱ ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች 17 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም በጨዋታ በአማካይ 2.8 ጎሎች መሆኑ ነው።

– ከ17 ጎሎች መካከል 12 ኳሶች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ወደ ጎልነት ሲቀየሩ ሦስት ጎሎች በፍፁም ቅጣት ምት፣ አንድ ጎል ከቀጥታ ቅጣት ምት፣ አንድ ጎል ከሳጥን ውጪ፣ አንድ ጎል በግንባር በመግጨት ተቆጥረዋል።

– ጎሎች ከተቆጠሩበት መንገድ ጋር በተያያዘ ከ17 ጎሎች መካከል አንድ ጎል (አብዲሳ ጀማል) ብቻ በጭንቅላቱ ገጭቶ ሲያስቆጥር ሌሎቹ ጎሎች በእግር ተመተው የተቆጠሩ ናቸው።

– በሳምንቱ የተቆጠሩት 17 ጎሎች በ13 የተለያዩ ተጫዋቾችተቆጠሩ ሲሆን አቡበከር ናስር፣ ታፈሰ ሰርካ፣ አብዲሳ ጀማል እና ፍፁም ዓለሙ ሁለት ጎሎች አስቆጠረው ቀሪዎቹ ዘጠኝ ተጫዋቾች አንድ አንድ አስቆጥረዋል። ሦስት ተጫዋቾች (አብዲሳ ጀማል፣ ዱላ ሙላቱ እና ያሬድ ታደሰ) ደግሞ ተቀይረው በመግባት ኳስ እና መረብ ያገናኙ ተጫዋቾች ናቸው።

– የአንደኛ ሳምንት ዲሲፕሊን ሪከርድን ስንመለከት በስድስት ጨዋታዎች 17 የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ ቀይ ካርድ ተመዘዋል። ይህም ከወትሮው ቁጥር በእጅጉ የቀነሰ ነው።

– ፋሲል ከነማ በአምስት ቢጫ ብዙ ካርድ በርካታ ካርድ የተመዘዘበት የሳምንቱ ቡድን ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ጨዋታ በሰባት ቢጫ ካርድ ከፍተኛውን ቁጥር ያስተናገደ ሲሆን ሰበታ ከተማ ምንም ካርድ ያልተመለከተ ቡድን ሆኗል።

ዕውነታዎች

– የዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ በ16 ቡድኖች መካከል ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ሦስት ቡድኖች ባለመሳተፋቸው በ13 ክለቦች መካከል ተጀምሯል። መሰል ክስተቶች በሊጉ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ አስተናግደዋል። በ1998 ሊጉ በ16 ክለቦች መካከል ሊካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም አርባምንጭ ጨጨ በመፍረሱ በ15 ክለቦች ውድድሩ ተጀምሯል። በ2000 ደግሞ በ14 ክለቦች መካከል ከተጀመረ በሁለት ወራት በኋላ 11 ክለቦች ተጨምረውበት በ25 ክለቦች መካከል ተካሂዷል።

– አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ወደ ክለብ አሰልጣኝነት ከተመለሱ ከረጅም ዓመታት በኋላ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል። ከ1996 የውድድር ዘመን ለመጨረሻ ጊዜ ወንጂ ስኳርን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዋና አሰልጣኝነት ከመሩበት ወቅት በኋላ አሰልጣኝ አብርሃም መብራህቱ በሰበታ ከተማ አሰልጣኝነት የሊግ ጨዋታ ሲመሩ ከ16 ዓመታት ከ6 ወር ከ9 ቀናት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሆኗል። 

– በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ከረጅም ዓመት የአሜሪካ ኑሮ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ባለፈው ዓመት ቡድናቸውን ከ16 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ቢመሩም ቢመሩም ሊጉ በኮቪድ መሰረዙ ይታወሳል።

– በአንደኛ ሳምንት ሽንፈት ካስተናገዱ ቡድኖች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጠቀሳል። ቡድኑ የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ጨምሮ ባለፉት አራት የውድድር ዓመታት የመክፈቻ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻለም። በሁለቱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ሲለያይ በሦስቱ ጨዋታዎች ደግሞ ጎል አላስቆጠረም።

– የዐምና ውጤቶች በኮቪድ ምክንያት በመሰረዛቸው ወልቂጤ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፍ ቡድን ሆኗል። ይህም 51ኛው የፕሪምየር ሊግ አዲስ ቡድን ማለት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ