ሪፖርት | በፍላጎት የተሻለው ኢትዮጵያ ቡና በጎዶሎ ተጫዋቾች ፋሲልን አሸንፏል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማን ከኢትዮጵያ ቡና ባገናኘው ጨዋታ 45 ያክል ደቂቃዎችን በ10 ተጫዋች የተጫወተው ኢትዮጵያ ቡና 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ፋሲል ከነማዎች ባሳለፈነው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታው ስብስብ ውስጥ ሁለት ለውጦችን አድርገው የገቡ ሲሆን በዚህም መሰረት ሳሙኤል ዩሀንስ እና በዛብህ መለዮ የመጀመሪያ ተመራጭ ሆነው የዛሬውን ጨዋታ መካተት ሲችሉ፤ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ከወልቂጤ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ የአራት ተጫዋችን ለውጦች አድርገዋል በዚህም ተመስገን ካስትሮ፣ ዓለምአንተ ካሣ፣ ሀብታሙ ታደሰ እና አቤል ከበደ በመጀመሪያ 11 በማካተት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

በርከት ባሉ የግብ ሙከራዎች የታጀበ ባይሆንም ሁለቱም ቡድኖች በነበራቸው የማጥቃት ፍላጎት የተሻለ እንቅስቃሴን አሳይተዋል። ነገርግን ሁለቱም ቡድኖች በሜዳኛው የላይኛው ክፍል በሚገኙ ተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ሁለቱም ቡድኖች ውጤታማ መሆን ያልቻሉበት አጋማሽ ነበር።

ፋሲል ከተማዎች ገና ከጅምሩ በቁጥር በርከት ብለው ተገማች የሆነውን የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ምስረታ ሂደት ለማቋረጥ ጫናን አሳድረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል ፤ በዚህም ጥረታቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ወደ ከአምስት በላይ የጨዋታ ቅፅበቶች በሜዳው የላይኛው ክፍል ኳሶችን መንጠቅ ቢችሉም በነበራቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ፍሬያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከፋሲል ከተማ የመጀመሪያ የጫና አጥር ጀርባ የሚገኙ ተጫዋቾን በረጃጅም ኳሶች በማግኘት ጥቃት ለመሰንዘር ፍላጎት አሳይተዋል በዚህም አጋማሽ የመጀመሪያውን ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ በ11ኛው ደቂቃ አለምአንተ ካሳ ካሻማውን የቅጣት ምት ተመስገን ካስትሮ ያሸነፈውን የመጀመሪያ ኳስ ተጠቅሞ አቤል ከበደ የሞከረ ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። በተመሳሳይ በ13ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው መሀል ሜዳ አካባቢ የተነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ ታፈሰ ከሳጥን ጠርዝ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጡበት ተጠቃሾች ናቸው።

በ34ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች አበበ ጥላሁን ወደ መሐል ሜዳ ከተጠጋ አቋቋም በረጅሙ ለታፈሰ ሰለሞን ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ታፈሰ ተቆጣጥሮ ከሳሙኤል ታፈሰ ጋር በመታገል የጨርፈው ኳስ ከመረብ ተዋህዶ ቡናማዎች ቀዳሚ መሆን ችለው ነበር።

ነገርግን የኢትዮጵያ ቡና መሪነት መዝለቅ የቻለው ለአራት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ38ኛው ደቂቃ ፋሲሎች በጥሩ የቅብብል ሒደት የተገኘውን አጋጣሚ በቡና ተከላካዮች መዘናጋት ታግዞ በዛብህ መለዮ ማራኪ ግብን ከሰጥን ውስጥ በማስቆጠር ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት አንድ አቻ በሆነ ውጤት እንዲያመሩ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ ተመስገን ካስትሮ ሙጂብ ቃሲም ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለተኛው አጋማሽን በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት ተገደዋል።

በቁጥር ያነሰ ተጫዋች ሜዳ ውስጥ ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ከፋሲል ከተማ የተሻለ ከጨዋታው መሉ ሦስት ነጥብ ይዘው የመውጣት ፍላጎት እንደነበራቸው አሳይተዋል።

በ55ኛው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ከፋሲል ተከላካዮች ጀርባ በነበረው ጥልቀት ያቀበለውን ኳስ አቡከር ናስር ያሬድ ባየን ተፈትልኮ በማምለጥ ከሚክኤል ሳማኪ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የመከናት ኳስ አስቆጭ ነበረች። በ58ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሂደት የተገኘችውን ኳስ አቡበከር ናስር ለመጠቀም ሲሞክር በሳማኪ ጥፋት ስለተሰራበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እራሱ አቡበከር ናስር መቶ በማስቆጠር ቡድኑን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በደቂቃዎች ልዩነት ታፈሰ ሰለሞን ያሰለፈለትን ኳስ አቡበከር ናስር ከፋሲል ግራ የሳጥን ጠርዝ ሰብሮ በመግባት በተሻለ አቋቋም ለነበረው ሀብታሙ ታደሰ ያሳለፈለትን ኳሶ ሀብታሙ ታደሰ በቀላሉ አስቆጥሮ የኢትዮጵያ ቡናን መሪነት ማሳደግ ችለዋል።

ከሁለቱ ግቦች መቆጠር በኃላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተሻለ ይንቀሳቀሳሉ ተብለው የተጠበቁት ፋሲል ከነማዎች በሁለት አጋጣሚዎች ሙጂብ ከመስመር ከተሻገሩ ኳሶች መነሻነት በግንባር በመግጨት ከሞከራቸው ኳሶች ውጭ እንደ ቡድን ይንቀሳቀስ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡናን የሁለተኛው አጋማሽ የመከላከል አደረጃጀት መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በዚህም ውጤት መሠረት ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ሲያስመዘግብ በሊጉ ጅማሮ ሁለት ተከታታይ ከባድ ጨዋታዎችን ያደረገው ፋሲል ከነማ ደግሞ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀምሷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ